የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ለንብረት ስም ዝውውር የታክስ ዕዳ ክሊራንስ (Clearance) ማስረጃ እንዲጠየቅ ደብዳቤዎች ፅፎ የነበረ ሲሆን እነዚህን ደብዳቤዎች መሻሩን ዛሬ ምሽት አሳውቋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው እና በዛሬው እለት በቢሮው ሃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ ለመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ ለመሬት ይዞታ መረጃና ምዝገባ ኤጀንሲ ፣ ለአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲደርስ ተደርጓል።
ለንብረት ስም ዝውውር የታክስ ዕዳ ክሊራንስ (Clearance) ማስረጃ እንዲጠየቅ ተወስኖ የነበረው በ20/08/17 ዓም እና 01/09/17 ዓም በተጻፉ ሁለት ደብዳቤዎች ነበር።
በዛሬው ዕለት የተላለፈው ውሳኔ ከዚህ ቀደም የተላለፉትን ሁለት ደብዳቤዎች በመሻር በነባሩ አሰራር እንዲቀጥል የሚያዝ ነው።
ደብዳቤው ከዛሬ ጀምሮ የታክስ እዳ ያለባቸው ግለሰቦች ብቻ ስማቸው ወደ አስፈጻሚ አካላት እንዲዛወር በማድረግ የታክስ ዕዳ ያለባቸውን ግለሰቦች በስም ዝርዝር በመላክ እየተጠራ የስም ዝውውሩ እንዲፈጸም መደረጉን ያሳውቃል።
ደብዳቤው በዝርዝር ምን ይላል ?
” ቢሮው ከታክስ ባለዕዳዎች የመንግስት ታክስ በአግባቡ ለመሰብሰብ እንዲቻል ከስም ዝውውር በፊት የታክስ ዕዳ ክሊራንስ ማስረጃ ማቅረብ የሚያስገድድ አሰራር ዘርግቶ ነበር፡፡
በዚህ አሰራር ማንኛውም ግለሰብ ኮድ 2 ተሸከርካሪ ወይም ለመኖሪያ፣ ለቅይጥና ለድርጅት አገልግሎቶች የሚጠቀምበት ወይም ያልተጠናቀቀ ቤት በሽያጭ ወይም በማንኛውም መንገድ የስም ዝውውር ከማከናወኑ በፊት የታክስ ዕዳ ነፃ ክሊራንስ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ ቆይቷል።
ይህ አሰራር የታክስ ዕዳ የሌለባቸው ግብር ከፋዮች እና የንግድ ስራ ላይ ላልተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎችን ላይ አላስፈላጊ እንግልት በመፍጠር የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠሩን አረጋግጠናል።
ቢሮው ችግሩን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለመቅረፍ የስም ዝውውር ከሚያከናውኑ ተቋማት ጋር በጋራ ኃላፊነት ለመስራትና በቴክኖሎጂ በመተሳሰር የታክስ ዕዳ ያለባቸውን ግለሰቦች በስም ዝርዝር በመላክ እየተጠራ የስም ዝውውሩ እንዲፈጸም የሚያስችል ሲስተም ለመዘርጋት እየሰራን ነው፡፡
በመሆኑም ቢሮው ተሽከርካሪ ወይም ቤት የሚሸጡ ግለሰቦች ከታክስ ዕዳ ነፃ መሆናቸው የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ እንዲሁም የአሽከርካሪና ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በቴክኖሎጂ በመታገዝ አጣርተው የስም ዝውውር መፈፀም እስኪጀምሩ ድረስ ቀደም ሲል በቢሮው የተፃፉ ደብዳቤዎች የተሻሩ በመሆኑ ተቋማቱ በነባሩ የስም ዝውውር አሰራራቸው አገልግሎት እንዲሰጡ እናሳውቃለን ” ይላል።
#TikvahEthiopiaFamilyAA
