ከእሸቱ ደስታ
ትምህርት ለአንድ ሐገር ወሣኝ የእድገት ምንጭ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በዚህም ዓለም ለትምህርት በተለይም “ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት የሚያምን ቢሆንም በአፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች የሚገኙ አገሮች ትምህርትን ለዜጐቻቸው በስፋት በተገቢው ሁኔታ አለማዳረስ በጥራት ለማካሄድ ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሀገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንቅፋት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
በሐገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለውን መጥቀስ ቢያስፈልግ ትምህርት ቤቶችን በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያለ ሙሉ ግብአት እና መምህራን መሟላት ከማስፋፋት ጐን ለጐን ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ይህም ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡
ሌላው በሐገራችን በተለይም በአማራ፣ በትግራይ እና በአንዳንድ ኦሮሚያ ክልሎች በታየው እና በሚታየው የሰላም እጦት እና የተለያዩ ችግሮች ምክንያት የመማር ማስተማር እድገት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለማሳያ ያህልም በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት ከ4.1 ሚሊየን በላይ ታዳጊ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተበትነዋል፡፡ በትግራይ ክልልም እንዲሁ ከ1.24 ሚሊየን በላይ ትምህርት ቤት መግባት የነበረባቸው ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ በሚሊየን የሚቆጠሩ ታዳጊ ልጆች የትምህርት እድል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሁለተኛ ደረጃ ፈተና ከተቀመጡት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት ተማሪዎች መካከል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ውጤት ያሟሉት ከሦስት በመቶ ያልበለጡት ናቸው፡፡
ይህም እስከአሁን ስናካሂድ የቆየነውን የትምህርት ሥርዓታችንን ውድቀት ከሚያንፀባርቁት ማሳያዎች አንዱ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ባለፉት ዓመታት በአንካሳው የትምህርት ሥርዓት አንድ ትውልድ ለፈተና መዳረጉን ብዙዎችን ያስማማል፡፡
ከዚህ በመነሳት አሁን የተጀመረው የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅ ተግባር የሚያበረታታ ቢሆንም በተቀናጀ ሁኔታ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ይህም የሁሉም ባለ ድርሻ አካላትን እንደ አንድ ሰው በመሆን መንቀሳቀስ ይገባል፡፡ ለዚህም ከታች ከአፀደ ሕጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ መሆን አለበት፡፡ የመጀመሪያው ተግባር መሆን ያለበት የመምህራኑን እውቀትም ሆነ ክህሎት የማረጋገጥ ተግባር ሲሆን ይህም በብቃታቸው እና ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ፤ በተባሉ ምሁራን መከናወን ይገባል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ ከኮሌጅም ሆነ ከዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ዲግሪ ከሚያገኙት ተማሪዎቻችን እና ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ጥቂት የማይባሉት የመመረቂያ ጽሑፎቻቸውን እንኳን የሚያዘጋጁት እነሱ ሳይሆኑ ከዚህ በፊት ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች በመውሰድ እና የስም ለውጥ በማድረግ በሌብነት በተደገፈ ማስረጃ መመረቃቸው ይመስለናል፡፡ በዚህም ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ሥራ ከተሰማሩት መካከል አንዳንዶቹ እራሳቸውን እንኳን መግለጽ የማይችሉ በወሬ ግንባር ቀደም የሆኑ እና በተግባር መሬት የወረደ ሥራ መስራት የማይችሉ መሆናቸውን መታዘባችን ነው፡፡ ይህም እየተደረገ ያለው በአንዳንድ የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚያስተምሩ ምግባረ ብልሹ መምህራኖችም ጭምር በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ተገቢው ክትትል እና ቁጥጥር መከናወን የግድ ይላል፡፡
የትምህርት ጥራታችንን ውጤታማ ካላደረግነው አንዱ እስከ አሁን በተለያዩ የትምህርት መስክ ተመርቀው ወደ ስራ አለም የተሰማሩትንም ሆነ ያልገቡትን መምህራን ተከታትይነት ያለው የሙያ መመዘኛ ስልጠና እና ብቃታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የመስጠቱን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሊታመንበት ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ስለ ትምህርት ጥራት ከማሰብ አልፎ ውጤታማነትን መጠበቅ አይቻልም፡፡
ብዙም ትኩረት ስላልተሰጠው የመምህርነት ሞያ ክብር እናንሳ፡፡ በዚህም በሙያው ከሚሰማሩት መምህራን መካከል ጥቂት የማይባሉት እንደ ስራ ሳይሆን እንደ መደበሪያ የሚቆጥሩት መሆኑ በብዙዎች ይደመጣል፡፡ ይህ ጉዳይ ታዲያ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሰራ አደጋው የከፋ ነው፡፡
ለመምህራን ከደመወዝ በተጨማሪ ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር ተብሎ በተለይ በአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ድጐማ እና በነጻ አንበሳ አውቶቡስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም አሁን ባለው የቤት ኪራይ ጭማሪ ምክንያት ወጣት መምህራን የምናገኘውን ደመወዝ የቤት ኪራይ እየበላብን ነው በሚል እሳቤ ተማሪዎችን በተገቢ ሁኔታ ከማስተማር ይልቅ በኑሯቸው ሲቆዝሙ ይታያሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በሌሎች አካባቢዎች በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በአፋር እና በጋምቤል አካባቢ ከተሰማሩ መምህራን የሚሰማው ሮሮ የወር ደመወዛቸው ጊዜውን ጠብቆ የማይከፈላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይሄንኑ አጥብቀው በሚጠይቁ መምህራን ላይ ደግሞ በአንዳንድ አመራሮች ዘንድ እንደ አድመኛ በመቁጠር ለእስር እንደሚዳርጓቸው በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃንም ይደመጣል፡፡ በተጨማሪ የሰላም እጦት ባለባቸው አንዳንድ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎችም ጭራሹኑ መምህራኑ ለደመወዝ ማሰብ ቀርቶ የመኖር ሕልውናቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የእለት በእለት ዜና ነው፡፡ ይሄ ችግር መንግስት ትኩረት ሰጥቶት በጊዜ እንዲፈታ ካላደረገ በአገራችን የመማር ማስተማሩ ላይ ትልቅ ጋሬጣ ይሆናል፡፡
በቅርቡ በአዲስ አበባ በትራንስፖርት ላይ ከአንዲት መምህር ጋር ስናወራ የነገረችኝን ላካፍላችሁ “የመጣሁት ከደቡብ ኢትዮጵያ ነው፡፡ 3 ልጆች አሉኝ፡፡ የባለቤቴ የወር ገቢ አነስተኛ በመሆኑ ይሄንኑ አዳምረን በምናገኘው ገቢ ከነ ቤተሰቦቻችን ኖርን ከተባለ እየኖርን ነው፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ የወር ደመወዛችን ጊዜውን ጠብቆ ባለመድረሱ ለመኖር እየተቸገርን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሙያውን ትቼ አረብ ሐገር ለመሄድ እየተዘጋጀሁ እገኛለሁ፡፡ ይህም እዚያ እየሰራው ቤተሰቤን ለማኖር የምችልበት አማራጭ የሌለው ውሣኔ ነው፡፡” ብላኛላች፡፡ እንግዲህ መምህርነትን የሚያክል ትልቅ ሙያ በመተው ለመሰደድ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ችግሩን አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ በሐገራችን የመማር ማስተማሩ ጉዳይ ላይ መንግስት በተለይም የሚመለከታቸው ሁሉ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ካልተንቀሳቀሱ በስተቀር የቁልቁለቱ መንገድ የከፋ ሆኖ ለወደፊቱ በሀገር ተረካቢ ወጣቶች ላይ ትልቅ ጋሬጣ እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 219 ሕዳር 28 ቀን 2017 ዓ.ም
