ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጥቅምት 26 ቀን 2018 ዓ.ም የአፋር ክልል ወሰንን አልፎ በክልሉ የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች ፈፅሞታል ሲል ክልሉ ከገለጸው ጥቃት ወዲህ “ በመቀሌ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ መደበኛ እንቅስቃሴ መቀዛቀዙን ” አዲስ ማለዳ ያነገጋገረቻቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ አንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት “ ጥቃቱ ተፈጽሟል ከተባለበት ጊዜ ወዲህ የቀደመው ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት ነዋሪዎች ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል ” ፤ “ አተርፍ ባይ” ሲሉ የገለጧቸው ነጋዴዎችም ሁኔታውን ተጠቅመው ለማትረፍ በምግብ እና ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ ይሸጥበት ከነበረው አንድ ሺህ አምስት መቶ (1,500) ብር አንድ ሺህ ስምንት መቶ (1,800) ብር ማሻቀቡን አመልክተዋል፡፡
በክልሉ ከሚመረቱ እና በቅርብ ከሚገኙ የአትክልት ምግቦች ባሻገር በሌሎች እንደ ማኮሮኒ፣ ሩዝና የመሳሰሉ ምግቦች ላይም ከ20 እስከ 30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል፡፡
“ ይህ በወንድማማች ህዝቦች መካከል በየጊዜው የሚነሳ ግጭትና ጦርነት ለምን ያስፈልጋል ” የሚል ጥያቄ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዳለ የተናገሩት አስተያየት ሰጪው በሸቀጦች ላይ ዋጋ ከመጨመር ባለፈ ምርቶቹ እየተደበቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ “ ከዚህ ቀደም የነበረውን ጦርነት ያውቀዋል፤ በቀደመው ጦርነት ያጣው አብሮ አደግ ወንድሙን ነውና በጭራሽ ወደ ጦርነት የመግባት ሀሳብ የለውም ”
የመቀሌ ከተማ ከሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት ለማገገም እንቅስቃሴ ላይ ባለችበት ሁኔታ የተከሰተው የባለፈው ሳምንት ጥቃት ዛሬ ላይ ከተማዋን ወደ መቀዛቀዝ እንደከተታትም ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ጦርነት ከተነሳ በሚል እያደረገ የሚገኘውን ቅድመ ጥንቃቄን ጠቅሰዋል፡፡ እሱም ገንዘብ ከባንክ በማውጣት ማስቀመጥ ሲሆን በዚህም በባንክ ቤቶች አካባቢ ረዣዥም ሰልፎች እና መጨናነቆች እንደሚታዩ ገልጸዋል፡፡
ከባንኮች በኩልም “ ጥሬ ገንዘብ (ካሽ) የለም ” የሚሉ ምላሾች እየተሰጡ መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪው ይህ ደግሞ ስጋት ማጫሩን አስረድተዋል፡፡
ይህን የጦርነት ደመና በመስጋትም ገንዘብ የሌለው ጭምር ከዚሀም ከዚያም ተበዳድሮ አስቤዛ ለመግዛት እየሞከረ መሆኑን ምሬት በተጫነው ድምጸት ተናግረዋል፡፡ “ የትግራይ ህዝብ ጦርነትን በውል ያውቀዋል፤ ዳግም እንዲቀሰቀስ አይፈልግም፤ ወጣቱም ራሱን ከዚህ እንዲያገል ” ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
“ ያለን ቁስል ይበቃናል፤ ሌላ አትጨምሩበን ” ያሉት ነዋሪ ሁሉም አካላት ጦርነቱ በማስቀረት፣ ወደ ስምምነት መምጣት በሚችልባቸዉ ሁኔታዎች ላይ መምከር አለባቸው ሲሉ ምክረሃሳበቸውን ለግሰዋል፡፡
የዚህ ስጋት መነሻ የሆነው ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ላይ በህወሓት ተፈጽሟል የተባለው ጥቃት ቢሆንም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግን መሠረተ ቢስ ሲል ውንጀላውን ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
የፌደራሉ መንግስት ቢያንስ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሁለቱን ክልሎች ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ያለው ነገር የለም፡፡
(አዲስ ማለዳ)
