በኢፈርት ኩባንያዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የባንክ ሂሳብ እግድ ተነሳ

Date:

በትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኢፈርት) ስር በሚንቀሳቀሱ 22 ኩባንያዎች የባንክ ሂሳብ ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ መነሳቱን ሰምታለች፡፡


በተቋሙ ኩባንያዎች የባንክ ሂሳብ ላይ የተጣለውን እግድ በሚመለከት አሰራርን በተከተለ መልኩ ለኢፈርት የደረሰው ደብዳቤ እንደሌለ እና እግዱ መነሳቱን ሂሳባቸው በታገደባቸው ኩባንያዎች አማካኝነት ለማወቅ መቻላቸውን ከኢፈርት አንድ ከፍተኛ ሃላፊ ሰምታለች፡፡


ጥቂት የኩባንያዎቹ ሃላፊዎች ወደ ባንኮች በመሄድ ባጣሩበት ወቅት በሂሳቦቻቸው ላይ ተጥሎ የቆየው እገዳ መነሳቱን መስማታቸውን፤ ነገር ግን ማን እንዳገደውም ሆነ በምን ምክንያት እንደታገደ እንዳልተገለጸላቸው አስረድተዋል፡፡

ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ግን ‹‹ከሽብር ጋር የተያያዘ ጥርጣሬ ስላለ መጣራት አለበት›› በሚል እገዳው መጣሉን መስማታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹የፍትህ ሚኒስቴር መሰል ጥርጣሬ ሲኖር በህጉ መሰረት ከ 3 ቀናት በላይ ማገድ አይችልም›› ያሉት ሃላፊዎቹ አሁን እገዳው ሙሉ ለሙሉ እንደተነሳላቸው መገንዘባቸውን ነግረውናል።


እነዚሁ ሰባት ሃላፊዎች የእግዱን መንስኤ ለማወቅ እንዲሁም እግዱ እንዲነሳ ለማድረግ ጥረቶችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት እኝሁ ከፍተኛ ሃላፊ፤ ከቀናት በፊትም እግዱ ስለመነሳቱ በቃል እንደተነገራቸው ተናግረዋል፡፡


ለችግሩ መፈታት በክልሉ መንግስት እና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተደረጉ ንግግሮች አስተዋጽኦ አድርገው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ታህሳስ 7 ቀን፤ 2018 ዓ.ም የፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ ዳባ ዋቅጅራ ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤም ሱር ኮንስትራክሽንን ጨምሮ በኢፈርት ስር የሚንቀሳቀሱ 22 ኩባንያዎች የባንክ ሂሳብ ህዳር 25 ቀን ፤ 2018 ዓ.ም እና ህዳር 30 ቀን፤ 2018 ዓ.ም ለሀገሪቱ ሁሉም ባንኮች የተፃፈ በተጻፉ ሁለት ደብዳቤዎች የሂሳብ እግድ መተላለፉን ያትታል።

ሆኖም በተቋማቱ ላይ የተጣለው እግድ በአዋጅ ቁጥር 1364/17 አንቀፅ 20/3 እግዱ እንዲነሳ ማዘዙን ለ30ዎቹም ባንኮች ታህሳስ 7 ቀን፤ 2018 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ ይገልፃል።


በደብዳቤው ላይ ፊርማቸው ያረፈው በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታውን አቶ ተስፋዬ ዳባ ዋቅጅራ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ሃላፊዎች ለማነጋገር ተደጋጋሚ የስልክ እና የአጭር የጽሁፍ መልእክት ሙከራ ብናደርግም፤ ምላሽ አልሰጡም፡፡


የትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኢፈርት) ከቀድሞ እና አዲስ ባለአደራ ቦርድ ጋር በተያያዘ ካለፈው አመት አጋማሽ ጀምሮ በፍርድ ቤት ክርክር ላይ ባለበት ወቅት፤ የድርጅቱ ንብረት የሆኑ ኩባንያዎች የባንክ ሂሳቦች ያለ ምንም የፋይናንስ ምርመራ ከኅዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በድንገት መታገዳቸውን “ሕገወጥ” ሲል ማውገዙ ይታወሳል፡፡ [ዋዜማ]

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...