በግዳጅ ልመና ላይ የተሰማሩ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ጥቆማ የተሰጣቸው አንዳንድ የጸጥታ አካላት ”የራስህ ስራ ላይ ለምን አታተኩርም” የሚል ምላሽ መስጠታቸውም በጥናቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ለግዳጅ ልመና እና ለሰዎች ዝውውር ወንጀል ስለመጋለጣቸው የሚዳስስና በዓይነቱ የመጀመሪያ የተባለ ጥናት ውጤት ይፋ ሆኗል፡፡ ይህ ጥናት በፖፑሌሽን ካውንስል እና በተባባሪ አካላት የተካሄደ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ሶስት ዋና ዋና ከተሞች፣ ማለትም (በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ እና በድሬዳዋ) ያለውን አስከፊ የወንጀል ሰንሰለት ያጋለጠ መሆኑ ተነግሯል።
የካቲት 10፣ 2018 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ይፋ የተደረገው ጥናቱ በግዳጅ ልመና ላይ የተሰማሩ ተጎጂዎች እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አጋልጧል። ተጎጂዎቹ ከማለዳው 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ድረስ እንዲለምኑ የሚገደዱ ሲሆን፣ ቀኑን ሙሉ የሚሰጣቸው ምግብም በጣም አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል።
ከሁሉ በላይ አስደንጋጭ የተባለው ግኝት ደግሞ፣ ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ህፃናቱ ለልመና እንዲመቹና የሰዎችን ርህራሄ እንዲስቡ በሚል ሆን ብለው ዓይነ ስውር እንደሚያደርጓቸው በጥናቱ መረጋገጡ ነው ተብሏል።
ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ተጎጂዎች መካከል ወደ ከተማ ሲመጡ ዓይናቸው ጤናማ የነበሩና አዘዋዋሪዎቹ “መድኃኒት ነው” በሚል ዓይናቸው ውስጥ በጨመሩባቸው አደገኛ ፈሳሾች ምክንያት የማየት ችሎታቸውን ሙሉ በሙሉ ማጣታቸውን በለቅሶ የተናገሩ እንዳሉ ተጠቅሷል። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ የሰው ንግድ ወንጀል ውስጥ ያለውን እጅግ ጨካኝ ገጽታ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ተጎጂዎች የሚሰበስቡትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለአዘዋዋሪዎች ለመስጠት እንደሚገደዱና ትዕዛዙን ባልፈጸሙበት ወቅት ግርፋትን ጨምሮ የተለያዩ አስከፊ አካላዊ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙባቸው በጥናቱ ተብራርቷል።
ጥናቱ የአካል ጉዳተኞች ከገጠር አካባቢዎች በደላሎችና በቅርብ ዘመዶች ጭምር እየተታለሉ ወደ ከተማ በመምጣት ለከፍተኛ እንግልት፣ ለጽኑ አካላዊ ጥቃትና ለግዳጅ ልመና እንደሚዳረጉ አጋልጧል።
ለግዳጅ ልመና የተጋለጡ አካል ጉዳተኞች በሚበዘብዟቸው ሰዎች ጥብቅ ክትትልና የሞት ዛቻን ጨምሮ በርካታ ማስጠንቀቂያ ስለሚሰነዘርባቸው ጉዳያቸውን ለፖሊስ የማመልከት ዕድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል። አብዛኞቹ ተጎጂዎች ከዚህ ህይወት ሊወጡ የቻሉት በታክሲ አሽከርካሪዎች፣ በጎረቤቶች ወይም በሌሎች መንገደኞች እርዳታ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።
በጥናቱ አንዳንድ የጸጥታ አካላት ጥቆማ በሚሰጣቸው ወቅት ተገቢውን እርምጃ አለመውሰዳቸውን አካቷል፡፡ በጥናቱ ቃለ መጠየቅ የተደረገለትና ከዚህ ቀደም ከነበረበት የአስገድዶ ልመና ሰለባነት መውጣት የቻለ አካል ጉዳተኛ በሰጠው ምስክርነት ”አንዳንድ ፖሊሶች ጥቆማ ሲሰጣቸው እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ እንደ ቅናት የሚቆጥሩ አሉ ማለቱ” በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
”ፖሊሶቹ ራሳቸው ’ለምን ስለ ሌላ ሰው ትጨነቃለህ?’ ዝም ብለህ ለራስህ ለምን አትሰራም? ብለው ይጠይቁኛል፡፡ ሰዎች ላንተ በቂ ገንዘብ ስለማይሰጡህ ነው ወይ? ይሉኛል፡፡ ለእነሱ ማስረዳት በጣም ብዙ ጊዜ ይፈጃል፤ አያዳምጡም፣ [ጥቆማው] የቅናት ይመስላቸዋል:: ከመረዳት ይልቅ ’የራስህ ስራ ላይ ለምን አታተኩርም’ ይሉኝ ነበር” በማለት ምስክርነት መስጠቱ በጥናቱ ተካቷል፡፡
በሌላ በኩል ጥቆማ የተሰጣቸው ሌሎች ፖሊሶች ወንጀለኞቹን አድነው መያዛቸውና ተጎጂዎቹም ከአስገድዶ ልመና ሰለባነት መውጣት መቻላቸው ተገልጿል፡፡
በጥናቱ ለችግሩ መፍትሄ እንዲሆን ከቀረቡ ነጥቦች መካከል፣ የአካል ጉዳተኞችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ በገጠር አካባቢዎች ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ መቀየር፣ ህግ አስከባሪ አካላት ስለ ጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እና ተጎጂዎች ከዚህ ህይወት ሲወጡ የሚረዱበት የመልሶ ማቋቋሚያ አገልግሎቶችን ማስፋፋት የሚሉት ይገኙበታል።
