ከጤና ተቋማት አጠገብ አገልግሎት የሚሰጡ ፋርማሲዎች፤ ከሚገኙበት አካባቢ 100 ሜትር እንዲርቁ የሁለት ዓመት ጊዜ እንደተሰጣቸው ኢትዮቲዩብ ሰምቷል።
ውሳኔው የመድኃኒት ሽያጭ አገልግሎትን ለሁሉም ማኀበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ሲባል በተዘጋጀው “የፋርማሲ ስታንዳድ” መሰረት የተወሰነ ነው ተብሏል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚ መሆን የጀመረውን “የፋርማሲ ስታንዳድ” ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ነው። ይህን ስታንዳርድ የማስፈጸም ኃላፊነት ደግሞ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ነው። ስታንዳርዱ የተዘጋጀው ፋርማሲዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር “ወጥ የሆነ አሰራር ባለመኖሩ” እንደሆነ ከባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የፋርማሲ ስታንዳርዱ ከመውጣቱ በፊት ፋርማሲዎች አገልግሎት የሚሰጡት እንደሚገኙበት ክልል በተለያየ መመሪያ ሲሆን አሁን ላይ የተዘጋጀው ስታንዳርድ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ፋርማሲዎች ወጥ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።
ኢትዮቲዩብ የተመለከተው ስታንዳርድ፤ “የፋርማሲ ባለሙያዎችን ኃላፊነት”፣ “ታካሚዎች ማግኘት ስለሚገባቸው አገልግሎቶች” እና “ፋርማሲዎች ሊኖራቸው ስለሚገባ የቦታ ስፋት እና ርቀት” የሚያብራራ ነው።
በዚህ መሰረት በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የተዘጋጀው ሰነድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ፋርማሲዎች ለታካሚዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡበት ሥፍራ የማዘጋጀት ግዴታ ጥሎባቸዋል። ይህ አሰራር ታካሚዎች ሚስጥራቸውን ጠብቀው ምክር ማግኘት እንዲችሉ ነው።
