የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ባካሄደው የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የዶላር የመሸጫ ዋጋ ካለፈው ሳምንት መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 18ኛው ዙር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ የአንድ የአሜሪካ ዶላር መሸጫ ዋጋ 155.12 ብር መድረሱን ገልጿል።
ባንኩ ለዚህ ጨረታ 70 ሚሊዮን ዶላር ለገበያ ያቀረበ ቢሆንም፣ ከተሳታፊ ባንኮች የቀረበው የፍላጎት መጠን ግን 145.31 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ ተመዝግቧል።
በዚህም መሠረት ዝቅተኛው የመቁረጫ ዋጋ 155.1200 ብር ሲሆን፣ አማካይ የጨረታ ዋጋው ደግሞ 155.1223 ብር ሆኖ አልፏል።
በጨረታው ላይ በአጠቃላይ 31 ባንኮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 21 ባንኮች በጨረታው አሸናፊ በመሆን የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ችለዋል።
በዕለቱ የቀረበው ከፍተኛው የመግዣ ዋጋ 155.1299 ብር ሲሆን፣ ዝቅተኛው ደግሞ 155.1010 ብር ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህም ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ከተካሄደው 17ተኛዉ ዙር ጨረታ የዶላር መሸጫ ዋጋ 155.05 ብር ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ጭማሪ የታየበት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
