በጦርነት ” የተመናመነው ” የትግራይ ህዝብ ዳግም ጦርነት ከተከፈተበት ” ህልውናው ” እንዳይጠፋ፣ አሁንም ቢሆን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳሰቡ።
ነዋሪዎች፣ በትግራይ ” የኤርትራ ሠራዊት በገፍ እየተጠጋ ” እንደሆነ እየገለጹ ናቸው፤ ሁኔታውን ተመልክታችሁት ነበር ? ያልናቸው የትንሳዔ ስርዓት ቃንጪ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ደጋፊ ጉድፈይ፣ ” አዎ። እያየነው፤ እየሰማነው ነው። የችግሩ ተጋፋጭ ነን፤ ህዝቡም የችግሩ ተጋፋጭ ነው ” ብለዋል።
” ‘ፅምዶ’ የሚሉት በሦተኛ ወገን በኤርትራ መንግስት እየተመራ ነው ብለን ነው የምናምነው። የተመራ ነው እንጂ ለትግራይ ህዝብ የሚጠቅምም አይደለም። ለኤርትራ መንግስትም ሰላም ነው እንጂ ጦርነት አይጠቅምም። ሆኖም ግን እንደዛ እየተካሄደ ነው ” ብለዋል።
ማንም ይምራው ማን ክልሉ “በፅምዶ” እየተረበሸ እንዳለ እንገነዘባለን ያሉት አቶ ደጋፊ፣ ” እየነገሩን እኮ ነው፤ ‘ፅምዶ ፈጥረናል፤ የትግራይ ህዝብ ተነስ፤ ተከላከል’ እየተባለ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል።
” የትግራይ ህዝብ በጦርነት ተመናምኗል። ህፃናት አልቀዋል፤ አሁንም ሊያልቁብን አይገባም። ይሄ ጦርነት ከተጨመረበት ደግሞ ጠቅላላ እንደ ህዝብ ይጠፋል ” ነው ያሉት።
መፍትሄውን በተመለከተ ምን አሉ ?
የክልሉ እና የፌደራሉ መንግስታት ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ አሳስበዋል፣ “በተለይ የህወሓት መሪዎች ከሻዕቢያ ለመዳን የትግራይን ህዝብ ምሽግ ማድረግን ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል” ነው ያሉት።
“ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው ሁሉም ነገር በሰላም ሲፈታ ነው። አሁንም በሰላም የመፍታት እድሉ ሰፊ ነው። የፕሪቶሪያው ውል በአግባቡ ስላልተፈጸመ ነው ችግር እየተፈጠረ ያለው” ባይ ናቸው።
ያልተፈጸሙት የትኞቹ የፕሪቶሪያ ስምምነቶች እንደሆኑ ስንጠይቃቸውም፣ “ለምሳሌ የትግራይ ክልል የነበሩ በኃይል የተያዙ መሬቶች አሉ። በምዕራብ ትግራይ የተያዘ ቦታ አለ። በኤርትራ መንግስት የተያዙ 57 የትግራይ ቀበሌዎች አሉ፤ ተይዞ ያለው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ተፈናቃዮችም እንዲመለሱ አሳስበው፣ ” ሠራዊቱ ራሱ በፕሪቶሪያ ውል መሰረት መቋቋሚያ ተሰጥቶት ወደመደበኛ ስራው እንዲመለስ ነው ተብሎ የነበረው፤ ይህ አልተደረገም። የፕሪቶሪያ ውል አቃፊ መንግስት መመስረት አለበት ይላል፤ ግን አልተመሰረተም፤ ህወሓትን አፍርሶ ህወሓት እየመራ ያለው” ሲሉም አክለዋል።
ስምረት ፓርቲ ምን አለ ?
በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ስምረት ፓርቲ በበኩሉ፣ ” በየከተማ ሻዕቢያ ገብቷል ” በማለት ” ህዝቡ ጦርነት ይከፈታል ብሎ በከፍተኛ ስጋት ” ላይ መሆኑን ገልጿል።
” እንደ ብልጽግናም የሚያውቁት ነው፤ እኛ እንደ ክልሉ የፓለቲካ ድርጅቶች ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነው” ያሉት አንድ የፓርቲው አካል፣ ” ሻዕቢያ በየከተማው ገብቷል፤ ህዝቡ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው ” ብለዋል።
በተያያዘ፣ ፓርቲዎቹ ምርጫን በተመለከተ ምን አሉ ?
የትንሳዔ ስርዓት ቃንጫ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ ” ይካሄዳል እያሉን ስላለ ምርጫ ቦርዱ ባዘዘው መሰረት ተዘጋጅተናል። ተወዳዳሪዎቹንም መልምለን ሰጥተናል።
ግን በትግራይ ስንት የምርጫ ክልል እና ምርጫ ጣቢያ እንዳለ አይታወቅም፤ በክልሉ ምርጫ በ2005 ዓ/ም እንደተቋረጠ ነው። የትግራይ ምርጫ ክልል ፓርቲዎች እንደ ሌሎች ክልሎች አልተሰጡም፤ ከተቋረጠበት ከ2005 ተነስተን ግን 38 የምርጫ ክልሎች ነበሩ ” ብለዋል።
ስምረት ፓርቲ በበኩሉ ፥ ምርጫ ለመወዳደር ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታ ማሟላቱን ገልጾ፣ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ “በክልሉ ውስጥ ምርጫው ይካሄዳል? አይካሄድም? የሚለው ጥያቄ ቀርቦለት እስካሁን ድረስ መልስ አልሰጠም” ብሏል።
” ይልቁንም የሻዕቢያ ወታደሮች በየከተማ ገብተዋል። ምርጫ ይደረጋል ተብሎ የሚታሰብ አይመስለኝም ” ያለው ፓርቲው፣ ይህን ማስፈጸም የሚችሉት የክልሉና የፌደራሉ መንግስታት መሆናቸውን ገልጿል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ጣቢያ እና የምርጫ ጽ/ቤቶች እንዲያሳውቀው ክልሉን ደጋግሞ ቢጠይቅም፣ እዳላሳወቀው መግለጹ ይታወሳል።
ያላሳወቀበት ምክንያቱን ለመጠየቅ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደን (ሌ/ጀ) ለመጠየቅ ሙከራ ያደረገ ሲሆን፣ እሳቸው ተደጋግሞ ተደውሎላቸው ስልካቸውን አላነሱም።
” ህወሓት ከሻዕቢያ ጋር ወግኗል ” ስለመባሉና ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሻቸውን ለማካተት ቲክቫህ ኢትዮጵያ ወደ አንድ የህወሓት አመራር ሙከራ ያደረገ ሲሆን፣ እሳቸውም ቀጠሮ ከሰጡ በኋላ ስልክ ሲደወል አላነሱም።
@tikvahethiopia
