በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳሬክቶሬት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በሰራተኞች መብቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የግብዓት የማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ድርጅት በተሰጠ ምክረ ሀሳብ መነሻነት፣የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት በንግድና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ።
ይህም መድረክ በሀገር ደረጃ ከሰራተኛ መብቶች ጋር የተያያዙ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲቻል ያዘጋጀው 10ኛው የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ነው፡፡
በዚህ በመድረክም የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ከፌዴራል እና ከሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በመድረኩ ተገኝተው የተጀመረው ስራ መልካም የሚባልና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት መብቶች ለማስከበር የሚቻልበትን መፍትሔ መስጠት የሚችል መሆኑን አስታውቀዋል።
