ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከዛሬ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ መከናወን ጀምሯል።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በምርጫው ድምፅ ለመስጠት በቅድሚያ በመራጭነት መመዝገብና የመራጭነት ካርድ መያዝ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ምዝገባው በአካልና በዲጂታል አማራጮች እየተከናወነ ይገኛል።
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ዕድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ፣ በምርጫ ክልሉ ቢያንስ ለ6 ወራት የኖረ ማንኛውም ዜጋ የመመዝገብ መብት አለው።
ይሁን እንጂ በአእምሮ ሕመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌላቸው፣ በእስራት ላይ ያሉ ወይም የመምረጥ መብታቸው በሕግ የተገደበ ሰዎች መመዝገብ አይችሉም።
ተመዝጋቢዎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት መያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ሰነድ የሌላቸው ደግሞ በታዛቢዎች ምስክርነት መመዝገብ ይችላሉ።
በተጨማሪም “ምርጫዬ” የተሰኘውን መተግበሪያና የፋይዳ ቁጥርን በመጠቀም በዲጂታል መንገድ መመዝገብና የመራጭነት ካርድን ማተም ይቻላል።
አንዴ የተመዘገበ መራጭ በማጭበርበር ካልሆነ በቀር ከመዝገብ እንደማይሰረዝ የታወቀ ሲሆን፣ ሁሉም ዜጋ ድምፁ ዋጋ እንዳለው ተገንዝቦ እንዲመዘገብ ጥሪ ቀርቧል።
