ባሳለፍነው እሁድ ነሐሴ 18/ 2017 ዓ/ም የኖርዌይ ዜግነት ያላት የ34 ዓመቷ የኦሮሞ ተወለጅ ታሚማ ንብራስ ጁሃር በኦስሎ ከተማ መገደሏ ተገለጸ። ተሚማ የተገደለችው በኦስሎ ከተማ በምትሰራበት “ጄምት” (Gemt) ተብሎ በሚጠራ የህፃናት ተራዕዶ ድርጅት ውስጥ መሆኑ ተዘግቧል።
ፖሊስ በተሚማ ግድያ የተጠረጠረ የ18 አመት ወጣት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ባለስልጣናት የገለጹ ሲሆን፤ ግለሰቡ በፖለቲካዊ ጥላቻ ወንጀሉን እንደፈፀመ መናገሩን እና የፅንፈኝነት ንግግሮችን ማድረጉን ገልጸዋል። ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ትውልደ ኢትዮጵያዊት የሆነችውን የኖርዌይ ዜጋ ግድያን ጨምሮ በሽብርተኝነት ወንጀሎች ክስ እንደቀረበበት አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ ተሚማ በህጻናት ተራዕዶ ስራ ላይ ሳለች መገደሏ “አሰቃቂ ድርጊት” ነው ሲል ግድያውን በጽኑ አውግዟል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ፤ በቤተሰቦቿ ላይ ለደረሰው ጥልቅ ሀዘን መጽናናትን ተመኝቷል። በተጨማሪም፣ ሁሉም ዜጎች በእኩልነትና ከጥቃት ነጻ ሆነው የመኖር መብታቸው እንዲጠበቅ ጥሪ አቅርቧል።
የቤተሰቧ ጠበቃ አኔቴ ሼርቨን አርኪቨን እንዳሉት፣ የተሚማ ቤተሰቦች ፍትህ እንዲረጋገጥ በመሻት የሚሟች ስምና ፎቶግራፍ ይፋ እንዲወጣ መደረጉን ገልጻለች። ጠበቃዋ አክላም፤ ተሚማ “ጥንቁቅና ሰዎችን የምታቀራርብ ሰው እንደነበረች” በመግለጽ ከተለያዩ የሙያ፣ የባህልና የሃይማኖት አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት መስርታ እንደነበር ተናግራለች።
ተሚማ መገደሏን ተከትሎ በኦስሎ ከተማ በሰፊው ቁጣና ሃዘን ተፈጥሯል። የካምፐን አካባቢ ነዋሪዎች የሻማ ማብራት እና የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ መርሃ ግብር ያደረጉ ሲሆን፣ በስፍራው የተገኙ ጓደኞቿና ዘመዶቿ “በዚህ አስቸጋሪና ጨለማ ጊዜ ውስጥ ሆነን የተሚማን የደግነትና የመልካም አርዓያነት ሕይወቷን እያስታወስን ፍቅራችንን እንገልጻለን” ብለዋል። ሕይወቷን የቀጠፈው አሰቃቂ ድርጊት ግን ከማንኛውም አስተሳሰብ በላይ ነው” በማለት ለተሚማ ያላቸውን ፍቅር ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኖርዌይ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በድርጊቱ መደንገጣቸውን በመግለጽ፣ ተገቢው ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።
እ.ኤ.አ በ1991 የተወለደችው ታሚማ ለቤተሰቧ የመጨረሻዋ ልጅ ነበረች። ኢትዮጵያ ከምትኖረው እናቷ ጋር በየቀኑ በስልክ ትነጋገር እንደነበት ተዘግቧል።
ታሚማ በልጅነቷ የገጠማትን አስቸጋሪ ሁኔታ ተከትሎ፣ የሕይወቷን ዓላማ ለህጻናትና ወጣቶች ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት የወሰነት ወጣት ነበረች። በኖርዌይ ኦስሎ በሚገኝ ኦስሎሜት ከተባለ ተቋም የልማት ጥናት ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን፣ በፍትህና በዘር እኩልነት ትግልም ተሳትፎ አድርጋለች።
ቤተሰቧ በህልፈቷ መራራ ሐዘን ውስጥ መውደቃቸውን ገልጸው፣ “የእሷ አለመኖር ጥልቅ ቁስል ጥሎብናል” ብለዋል። የኖርዌይ መንግስት የግድያውን መንስኤ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ አሰቃቂ ድርጊት እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። “ተጠያቂነት ነገም እንደዚህ አይነት ጥቃት በሌሎች ላይ እንዳይደርስ ለመከላከል ወሳኝ ነው” ሲሉም አክለዋል።
በተጨማሪም ቤተሰቦቿ በሰጡት መግለጫ፣ “ኖርዌይ የትኛውንም ዘርና ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች በሰላም የሚኖሩባት አገር ሆና መቀጠል አለባት” በማለት ለኖርዌይ ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ግድያ የዘረኝነት እና የጥላቻ አደገኛነት ትልቅ ማሳያ መሆኑን በመግለጽ፣ እኩልነትንና መተባበርን ለመጠበቅ ሁሉም በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።አስ
