ኮከቡ እየ
ትውልደ ኢትዮጵያዊው የዓለም ዋንጫ ኮከብ አሊ አህመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ለመግባት በአውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
የ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ታሪክ የሰራውና በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ሀገር ለሚገኘው ታሪካዊው ክለብ ኖርዊች ሲቲ (Norwich City F.C.) በመጫወት ላይ የሚገኛው ድንቅ አማካኝ አሊ አፈንዲ አህመድ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ወላጆቹ የትውልድ ሀገር ኢትዮጵያ ለመግባት በአሁኑ ሰዓት አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
ተጫዋቹ ወደ እናት ሀገሩ እየተጓዘ መሆኑን የሚያሳይ ምስል በይፋዊ የኢንስታግራም ገጹ (Instagram Story) ላይ ያጋራ ሲሆን፣ ይህ ታሪካዊ የመጀመሪያ ጉብኝቱ ለሀገር ውስጥ ስፖርት አፍቃሪያን እና ለወጣት ተጫዋቾች ታላቅ መነሳሳትን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
አሊ አህመድ በሜጀር ሊግ ሶከር (MLS) ከቫንኩቨር ኋይትካፕስ ጋር አስደናቂ ጊዜን ካሳለፈ በኋላ፣ በፈረንጆቹ ጃንዋሪ 2026 ወደ እንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ በይፋ የተዛወረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በክለቡ የማሊያ ቁጥር 21 በመልበስ በክንፍ እና በአማካኝ ስፍራዎች ላይ የቡድኑ ቁልፍ ተሰላፊ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።
በ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ አሊ አህመድ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የዘር ግንድ ኖሮት በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ የተጫወተ ታሪካዊ ኮከብ በመሆን ስሙን በክብር መዝገብ ላይ አሳርፏል።
በምድብ ማጣሪያው ካናዳ ከቦስኒያ ሄርዜጎቪና፣ ኳታር እና ስዊዘርላንድ ጋር ባደረገቻቸው ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን፣ የካናዳ ብሔራዊ ቡድን እስከ 16ቱ ዙር ድረስ ተጉዞ በሞሮኮ እስከተሰናበተበት እለት ድረስ ለአለም እግር ኳስ አፍቃሪዎች የራሱን ልዩ ፈጣን እና ቴክኒካዊ ብቃት አሳይቷል።
በ2000 እ.ኤ.አ በካናዳ ቶሮንቶ የተወለደው የ25 ዓመቱ አሊ፣ ወላጆቹ አቶ አፈንዲ እና ወይዘሮ ሙና ከ30 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል (ከምስራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በዴሳ ከተማ) ተነስተው ወደ ካናዳ ያቀኑ ጠንካራ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
አሊ በካናዳ ቢያድግም ከቤተሰቦቹ ጋር ባለው ጥብቅ ትስስር ምክንያት እንግሊዘኛን ጨምሮ የኦሮሚኛ ቋንቋን (Afaan Oromoo) አቀላጥፎ መናገር ይችላል።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሙ የናኘው ድንቅ ወጣት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት እጅግ የሚያስደስት ሲሆን፣ በወደፊት የስፖርት ህይወቱ ይበልጥ እንዲያበራ እና ደመቅ ያለ ውጤት እንዲያስመዘግብ ሙሉ ስኬትን እንመኝለታለን።
