አሜሪካዊው ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት በዓለም ዙሪያ 1.4 ቢሊዮን አማኞች ያሏት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተመረጡ።
አሜሪካዊው ካርዲናል ሮበርት ፕሪቮስት በዓለም ዙሪያ 1.4 ቢሊዮን አማኞች ያሏት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተመረጡ።
የ69 ዓመቱ ሮበርት ፕሬቮስት ለርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳትነታቸው ሊዎ 14ኛ የሚለውን ሥም ወስደዋል።
በቫቲካን ቅዱስ ጴስሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕምናን እና ታዳሚያን ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባሰሙት ንግግር “ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለዋል።
“ውድ ወንድሞች እና እህቶች ይህ የተነሳው ክርስቶስ፣ ሕይወቱን ለእግዚዓብሔር መንጋ የሰጠው የመልካሙ እረኛ የመጀመሪያ ሰላምታ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል። “እኔም ይህ የሰላም ሰላምታ ወደ ልባችሁ እንዲገባ፤ ከቤተሰቦቻችሁ፣ በየቦታው ላሉ ሰዎች ሁሉ ይደርስ ዘንድ እወዳለሁ። ሰላም ለእናንተ ይሁን” ሲሉ ምዕምናን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ደስታቸውን ገልጸዋል።
በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ሆነው ባሰሙት አጭር ንግግር “ያለ ፍርኃት፣ በአንድነት ከእግዚዓብሔር እና እርስ በርሳችን እጅ ለእጅ በመያያዝ ወደፊት እንራመድ” የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል።
በንግግራቸው የቀድሞውን የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አመስግነዋል።
ከምርጫው በኋላ የዓለም መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎ የደስታ መልዕክት እያስተላለፉ ነው።
