የተሟላ የሂሳብ መዝገብ ለማያቀርቡ 15 በመቶ ግብር ተቀናሽ ይደረጋል

Date:


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2018 የግብር ዓመት የታክስ ሂሳብ መግለጫዎች ግብርን ለማሳወቅ ሲቀርቡ የግብርና ታክስ አሰባሰብ ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ለማድረግ የሚያስችል የዴስክ ኦዲት (Desk Audit) ማስፈጸሚያ(Guideline) ማዘጋጀቱን አስታወቀ።

​ቢሮው ባወጣውና ሰነድ ፣ በተለይም የደረጃ «ሀ» ግብር ከፋዮች የሚያቀርቧቸውን የሂሳብ መዛግብት በጥራትና በፍትሐዊነት ለመመርመር እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የታዩ ክፍተቶችን ለማረም ማስፈጸሚያው ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብሏል።

በ2017 በጀት ዓመት የታክስ ሂሳብ መግለጫዎች ላይ በተደረገ ግምገማ፣ በርካታ ግብር ከፋዮች አጥጋቢ ያልሆነ የገቢ ማስታወቂያ በማቅረብ ቢሊዮን ብር የሚገመት ገቢ አሳንሰው ማስታወቃቸው መረጋገጡን ጠቅሶ፤ ይህን መሰል ህገ-ወጥ አሰራርና የገቢ ማሳነስን ለመግታት ወጥ የሆነ የኦዲት ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋቱን አስረድቷል።

በማስፈጸሚያ ሰነዱ ውስጥ ከተካተቱ ነጥቦች መካከል በባንክ ሂሳባቸው የሚታየውን ያልተገለጸ ከፍተኛ ገንዘብ “የእቁብ ነው” በማለት ምክንያት ለሚያቀርቡ ግለሰብ ግብር ከፋዮች ጥብቅ ማስረጃ አስገዳጅ ማድረግ አንዱ ነው።

ግብር ከፋዮቹ :-

– የእቁብ ሰብሳቢና ዳኛ የተፈረመበት ማስረጃ፣

– የእቁብተኞች ዝርዝር፣

– የእቁብ ደብተር፣ እንዲሁም እቁቡ በዕጣ ወይም በግዢ መገኘቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ ካልቻሉ ገንዘቡ እንደ ንግድ ገቢ ተቆጥሮ ግብር ይጣልበታል።

የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ (ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም) ከሚያገኙት ማስታወቂያና ስፖንሰርሺፕ በተጨማሪ፣ ከተከታዮች በቀጥታ ሥርጭት (Live streaming) ወቅት የሚሰጡ ስጦታዎችና ስታሮች (Gifts/Stars)፣ የብዙሃን የገንዘብ ድጋፍ (Crowdfunding) እና የደንበኝነት ክፍያዎች (Membership Fees) ግብር እንደሚከፈልባቸው ተመላክቷል።

የተሟላ የሂሳብ መዝገብ ለማያቀርቡ የይዘት ፈጣሪዎች ከጠቅላላ ገቢያቸው ላይ 15 በመቶ ግብር ተቀናሽ ይደረጋል።

ለዲጂታል ይዘት አመንጪዎች ክፍያ የሚያመቻቹ መድረኮች (platforms) ለእያንዳንዱ የዲጂታል ይዘት አመንጪ የተከፈለውን ገንዘብ የሚያሳይ ሪፖርት ለታክሱ ባለስልጣን የመላክ ግዴታ አለባቸው ተብሏል፡፡

ልኳንዳ ቤቶች የሚያቀርቡት የሽያጭ መጠን ከቄራዎች በሚገኝ የ3ኛ ወገን የዕርድ መረጃ (የታረዱ ከብቶች ብዛትና ዓይነት) በሲስተም ተመሳክሮ ኦዲት ይደረጋል።

ስጋ ቤቱ ካሳወቀው ሽያጭ በላይ እንስሳትን ያሳረደ ሆኖ ከተገኘ፣ ልዩነቱ በአካባቢው የገበያ ዋጋ ተሰልቶ ወደ ሽያጭ እንዲለወጥና ግብር እንዲከፈልበት ይወሰናል።

የስራ ተቋራጮች በሂሳብ መዝገባቸው የሚያስመዘግቧቸው ወጪዎች ፕሮጀክቱ ካለበት የግንባታ ምዕራፍ ጋር የሚፈተሹ ሲሆን ለማሳያነትም፦

° በቁፋሮ ደረጃ ላይ ላለ ፕሮጀክት ከፍተኛ የሲሚንቶና የብረት ወጪ፣ ወይም

° በፊኒሺንግ (ማጠናቀቂያ) ላይ ላለ ህንፃ የኤክስካቫተር እና የአፈር ገልባጭ መኪና ኪራይ ወጪ ተደርጎ ከቀረበ ተቀባይነት እንደማያገኝ ተገልጿል።

ህንፃ አከራዮች ከእርጅና ቅናሽ ወጪ በፊት ያለውን ትርፍ ገንዘብ ከንግዱ አውጥተው በግል ለመጠቀም የሚያቀርቡት መከራከሪያም ገደብ ተበጅቶለታል።

በተጨማሪም የህንፃው የተከራየበትና ያላለቀ ክፍሎች፣ እንዲሁም ባዶ የሆኑት ወይም ለግል አገልግሎት የዋሉት ክፍሎች በካሬ ሜትር በግልጽ በማስረጃ መለየት እንዳለባቸው ታዟል።

መኪና አስመጪዎች ለእያንዳንዱ የተሸጠ መኪና የቆረጡት የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ እና ወደ ባንክ ገቢ የተደረገበት ቀንና የገንዘብ መጠን ካልተጣጣመ፣ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ጥናት መሰረት ግብር እንዲከፍሉ ይደረጋል።

​ቢሮው ያወጣው ይህ ዝርዝር ማስፈጸሚያ (Guideline) ፣በግብር ከፋዮች ዘንድ በተለያዩ የሂሳብ ማጭበርበሪያ ዘዴዎች ይሸሸጉ የነበሩ ገቢዎችን በመረጃና በቴክኖሎጂ አስደግፎ ወደ ታክስ መረቡ ለማስገባት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

@tikvahethiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ10 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ጥቅምት 12 ቀን 2019...

ዳሸን ባንክ እና ሼባ ማይልስ የፕላቲንየም ብራንድ የማስተር ካርድ ይፋ አደረጉ

ዳሸን ባንክ እና ሼባ ማይልስ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ደንበኞች የፕሪሚየም...

የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊ ኢራንን አስጠነቀቁ

ቡሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን አርብ ዕለት ኢራን በውጭ...

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ  በአመት ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታጣለች

85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን...