በኢትዮጵያ እየጨመረ በመጣዉ የህዝብ ቁጥር ምክንያት በመጪዎቹ ዓመታት ለ67 ሚሊዮን የሚሆኑ አዳዲስ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግዴታ እንደሚኖርባት አዲሱ የአለም ባንክ መረጃ አመላከተ።
ይህም በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ከናይጄሪያ እና ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቀጥሎ ኢትዮጵያን በሦስተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ የሚያደርግ ከፍተኛ ፈተና ነው።
የዓለም ባንክ በሰጠው መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ በተለይም እኤአ እስከ 2050 ዓ.ም. ድረስ በ15-64 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የሥራ ዕድሜ ህዝብ ቁጥር ዕድገት እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ ይህን ያህል ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠርን ይጠይቃል።
ተቋሙ የዚህን ፈተና መክበድ ምክንያት ሲያብራራ “የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው አጥጋቢ አለመሆን እና ፈጣን የህዝብ ቁጥር መጨመር” መሆኑን አክሏል።
ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ፣ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከታንዛኒያ እና ከዩጋንዳ ጋር በመሆን በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ከሚጠበቀው አጠቃላይ የሥራ ዕድል ፈተና ግማሽ ያህሉን የሚሸፍኑ አምስቱ ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች።
የአለም ባንክ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ አፍሪካ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ለእያደገው ህዝቧ የሚፈለገውን ያህል ቋሚ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመፍጠር እየተቸገረች ነው። ይህም ወደ ከፍተኛ የችሎታ በታች መሥራት፣ ያለፍላጎት በግል ሥራ መተዳደር እና መደበኛ ባልሆነ የሥራ ዘርፍ መመደብ ምክንያት ሆኗል ሲል አስታውቋል።
CapitalNews
