ይህ ግዙፍ ግድብ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን፣ ይህም ለበርካታ የአገሪቱ ዜጎች የኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲያዩ ዕድል እንደሚፈጥር ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ መንግሥት 46 በመቶ የሚሆነው የኤሌትሪክ የማያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ የጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገለፀዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት 54 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
“46 በመቶ ያህሉ አሁንም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተጠቃሚ አይደለም። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይህንን ቁጥር ለመቀነስ ነው እየሠራን ያለነው።”
ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅድ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2030 ቢያንስ 90 በመቶ የአገሪቱ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት በአፍሪካ ግዙመሆኑ እየተነገረለት ያለው የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታው በአምሰት ዓመት ይጠናቀቃል ቢባልም 14 ዓመታትን ፈጅቷል።
ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ይህ ግድብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የተገነባው በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ ነው” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ለመገንባት ከአሜሪካ ድጋፍ ማግኘቷን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባችው በአብዛኛው በአሜሪካ ገንዘብ ነው” ቢሉም አገራቸው መቼ እና በምን መልኩ ገንዘቡን እንደሰጠች ያሉት ነገር ግን የለም።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ይህ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ገንዘብ ነው የተገነባው” በማለት አገሪቱ ከየትኘውም ወገን የገንዘብ ድጋፍ ሳታገኝ በሕዝቧ እና በራሷ አቅም መገንባቷን በተመለከተ ሲነገር የቆየውን አረጋግጠዋል።
ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ግድቡን ለመገንባት ስለተገኘ ገንዘብ የሚሰጡ አስተያየቶችን በተመለከተ ሲናገሩም “ይህ ውሸት ነው” በማለት “በኢትዮጵያውያን ንፁህ ገንዘብ ገንብተን፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ ለምረቃ የሚበቃው” ብለዋል።
አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ወጪን የጠየቀው ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ የተገነባው ሕዝቡ ባወጣው ገንዘብ እና አገር ውስጥ ባለ ሃብት መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብቱን ያፈሰሰበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ለግድቡ ድጋፍ አድርገናል የሚለው አስተያየትን ትክክል ያልሆነ በማለት ውድቅ አድርገዋል።
