ኢትዮጵያ ከ50 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትን ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመርጣለች

Date:

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን የዓለማችን ዋነኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ፀባይ ለውጥ ጉባኤን እንድታስተናግድ ብራዚል ውስጥ እየተካሄደ ባለው የዘንድሮ ስብሰባ ላይ ተመረጠች።

ኮፕ በመባል የሚታወቀውን እና በየዓመቱ ከሚካሄደውን የአየር ፀባይ ለውጥ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ 2027 የሚደረገውን “ኮፕ32” ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ናይጄሪያን በመብለጥ ነው።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2027 የሚካሄደውን ጉባኤ በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ የአፍሪካ አገራትን ድጋፍ አግኝታለች።

ኮፕ የሚለው ስያሜ ‘ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ’ የሚሉት ቃላት ምህጻረ ቃል ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ፀባይ ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ስር የሚካሄድ የዓላማችን ዋነኛው የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ነው።

በጉባኤው ከአሜሪካ በስተቀር (አሜሪካ በትራምፕ አስተዳደር ራሷን አግልላለች) መላው የዓለም አገራት እና ሌሎችም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙ ሲሆን፣ ወሳኝ ድርድሮች እና ስምምነቶች የሚደረሱበት ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ ለማዘጋጀት መመረጧ በጉባኤው አጀንዳ ላይ እና በማብቂያው ላይ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ሚና እንዲኖራት ያደርጋል።

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሉልሰገድ ታደሰ ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታስተናግድ መመረጧን አስመልክቶ ባሰሙት ንግግር ” በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ እምነት ስለተጣለ እናመሰግናለን ” ብለዋል።

ሰላሳኛው የኮፕ ጉባኤ በብራዚሏ ቤሌም ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ የቀጣዩን ዓመት ጉባኤ አውስትራሊያ እና ቱርክ ለማስተናገድ እየተፎካከሩ ነው። 31ኛውን የኮፕ ጉባኤ አስተናጋጅ በቀጣዮቹ ቀናት ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።

አሁን ብራዚል ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው ኮፕ 30 ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከዓለም ዙሪያ 50 ሺህ በላይ ሰዎች ለመሳተፍ ተመዝግበዋል።

በጉባኤው ላይ፦
– ጋዜጠኞች፣
– የአየር ፀባይ ሳይንቲስቶች፣
– የቀደምት ማኅበረሰብ መሪዎች እና የ195 አገራት ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢ ጥበቃ ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ይገኛሉ።

የ2027ቱን ጉባኤ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዛፍ ችግኞችን እየተከለች እና ግዙፍ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን እየገነባች ነው። በዚህም በአካባቢ ጥበቃ በኩል ስሟ ግሎቶ ይጠቀሳል።

ይህን መረጃ ሮይተርስን ዋቢ በማድረግ ያስነበበው ቢቢሲ ነው።

@tikvahethiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ምንገድ ላይ

(በእውቀቱ ስዩም) በቀደም ከሆነ ቦታ ተነስቼ ወደ አልሆነ ቦታ ስራመድ...

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በጡረታ ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ...

አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ አዲስ መግለጫ አወጣች

ታዋቂዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ለስፖርት ወዳጆችና ለደጋፊዎቿ ወቅታዊ መረጃ...