ከዛሬ ሃያ አመት በፊት በደራሲ አውጉቸው ተረፈ ( ህሩይ ሚናስ) አማካኝነት እንድ ወጣት ከመፅሐፍ ንግድ ጋር ተዋወቀ:: ይህ ወጣት ህይወቱን ለማሸነፍ ብሔራዊ ቴአትር አካባበቢ አስፓልት ዳር አሮጌ መፅሐፍትን በመሸጥ የመፅሐፍ ስራን አንድ ብሎ ጀመረ::
የእለት ኑሮውን ለማሸነፍ መንገድ ዳር ላይ አሮጌ መፅሐፍት መሸጥ የጀመረው ይህ ወጣት ወደፊት የመፅሐፍት ንግድ መተዳዳሪያዬ ይሆናል ብሎ በጭራሽ አስቦ አያውቅም::
በዚህ መልኩ የመፅሐፍትን መሸጥ የጀመረው ይህ ወጣት ከመፅሐፍት ገዢዎችና አንባቢያን ጋር ባለው ትህትና የተላበሰ መግባባትና መቀራርብ በአጭር ጊዜ ከበርካታ የመጽሐፍ አንባቢያን እና ደራሲያንን ደንበኛ እና ወዳጅ ለማድረግ ቻለ::
ብዙም ሳይቆይ ከሁለት ዓመት በኃላም ወረት ያዘ:: እዚያው ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ አንድ አነስተኛ ሱቅ ተከራየ:: የመፅሐፍ መደብሩንም በራሱ ስም ሰየመው:: በመፅሐፍ መደብሩም ከአሮጌ መፅሐፍ በተጨማሪም አዳዲስ መፅሐፍትን ከአከፋፋዬች እና ከደራሲያን እየተረከበ መሸጥ ቀጠለ:: ከዚያማ እውቅናው ጨመረ :: የበርካታ ደራሲያንን መፅሐፍ የማሳተምና የማከፋፈል ተግባር የወጣቱ ዘወትር ተግባር ለመሆን ቻለ::
በሐገራችንም በመፅሐፍ ሕትመትና ስርጭት ተግባር የዚህ ሰው ስም ከመፅሐፍ መደብሩ ጋር በመፅሐፍ አንባቢያንና ፀሐፊያን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታወቅ ሆነ:: በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የመፅሐፍ መደብሮችን ከፍቶ መፅሐፍትን በማሳተምና በማከፋፈል እየሰራ ይገኛል::
ህይወቱን ለማሸነፍ ብሔራዊ ቴአትር አካባበቢ አስፓልት ዳር አሮጌ መፅሐፍትን በመሸጥ ስራ ጀመረው የትላንቱ ወጣት የዘሬው ጎልማሳ አሳታሚ: አከፋፋይ እና የበርካታ መፅሐፍ መደብሮች ባለቤት የሆነው ሰው ጃፋር ሺፋ ይባላል:: የመፅሐፍ መደብሩም “ጃፋር የመጽሐፍ መደብር”ይሰኛል::
ከሃያ አመት በላይ መፅሐፍን በማሳተም በመሸጥና በማከፋፈል ስራ ላይ ያለው ጃፋር ሺፋ ህይወቱን ከመፅሐፍ ስራ ውጪ ማሰብ አይችልም:: ለዚህም ነው የመፅሐፍ መደብሮቹ ቁጥር በዝተው በመላው አዲስ አበባ ዙሪያ በርክተው የምናያቸው::
ዛሬ ደግሞ ጃፋር ሺፋ በአዲስ ነገር ተከስቶአል:: በሌለው ዓለም የምናያቸውንና የምንቀናባቸውን አይነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን በስፋቱ እጅግ ግዙፉ እና ዘመናዊ የሆነውን ጃፋር የመጻሕፍት መደብር (Jafar Book Store) ለገሐር በተወልደ ህንፃ ምድር ላይ ሊከፍትጥቂት ቀናት ቀርተውታል::
እኔም ይህንን 300 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ግዙፍና ዘመናዊን የመፅሐፍ መደብር (Jafar Book Store)ን ጃፋር ከሳምንት በፊት እንድጎበኝው ጋብዞኝ ጎብኝቼዋለሁ::
በዚህ ግዙፍ የመፅሐፍ መደብር ውስጥ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩንቨርስቲ ድረስ የትምህርት መርጃ መጻህፍት፣ የሐገር ውስጥና የውጭ የልብወለድ መፅሐፍት ፣ የታሪክ መጻህፍት፣ ኢንሳይክሎፒድያ ፣ መንፈሳዊ መጻህፍት፣ የግጥምና የወግ መጻህፍት፣በሐገር ውስጥና በውጭ ፀሐፊያን በእማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፉ የፖለቲካ ፣ ኢኮኖሚ ፣ የቋንቋ የፍልስፍና ፣ የስነልቦና መጻህፍት፣ እንዲሁም የህፃናት መፅሐፍት በየኮርነራቸው ተደርድዋል::
መፅሐፍ መደብሩ ሙሉው የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት ሲሆን መፅሐፍ ለመግዛት ወደ መደብሩ የሚመጣ ሰው ልክ እንደ ሱፐር ማርኬት የሚፈልገውን መፅሐፍት መርጦ ከጨረሰ በኃላ ግብይቱ የሚካሄደው በዲጂታል ቴክኖሎጂ መፅሐፉ ላይ ያለውን ባር ኮድ እስካን በማድረግ ነው :: ይህን ግዙፍና ዘመናዊ የሆነውን የመፅሐፍ መደብር ለመፅሐፍ ወዳጆች ለደራሲያንና ለአንባቢያን ልዩ ትርጉም የሚሰጥ ይመስለኛል::
ከ ሃያ ዓመት በፊት በመንገድ ላይ አሮጌ መፅሐፍ በመሸጥ ከመፅሐፍ ጋር የተዋወቀው ጃዕፈር ሺፋ ዛሬ በስፋቱ እጅግ ግዙፉ የሆነውን እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለለትን ዘመናዊ የመፅሐፍ መደብር በከተማችን ውስጥ ለመክፈት በመብቃትህ ምስጋናዬ ይድረስህ እንኳንም ደስ ያለህ ለማለት እወዳለሁ::
በመሆኑም ግዙፉን እና ዘመናዊውን የመፅሐፍ መደብር የፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ደራሲያን የኪነጥበብ ባለሙያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ያስመርቃል:: እኛም በእለቱ ተገኝተን እንመርቃለን::
(ይትባረክ ዋለልኝ)
