ከኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ መመዝገቢያ ሥርዓት አስገዳጅ የሚያደርግ መመሪያ ወጥቷል

Date:

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ አስተዳደሩን ለማዘመን እና የታክስ ስወራን በዘላቂነት ለመከላከል ያስችላል ያለውን “የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1142/2018” አውጥቷል።

መመሪያው በዋናነት የታለመው የታክስ አስተዳደሩን ከዘመናዊው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ለማጣጣም ነው።

እንደ መመሪያው ገለጻ፣ ማንኛውም የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ያለበት ታክስ ከፋይ በሚኒስቴሩ እውቅና ከተሰጠው የሽያጭ መመዝገቢያ ሶፍትዌር ጋር የተገናኘ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ የመጠቀም ግዴታ ይኖርበታል።

ይህ አሰራር ግብይቶች በተከናወኑበት ወዲያውኑ (Real-time) ለሚኒስቴሩ ማዕከላዊ የመረጃ ቋት ሪፖርት እንዲደረጉ የሚያስችል በመሆኑ፣ መረጃዎችን የመሰወርና ደረሰኞችን የማጭበርበር እድልን በእጅጉ እንደሚያጠፋው ይጠበቃል።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት፣ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ የሚሰጠው በሚኒስቴሩ ተገንብቶ በሚቀርበው ማዕከላዊ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ መመዝገቢያ ሥርዓት አማካኝነት ነው።

እያንዳንዱ ደረሰኝ የደረሰኝ ምዝገባ ቁጥር (IRN) እና ፈጣን መላሽ ኮድ (QR Code) የሚሰጠው ሲሆን፣ ይህም ደረሰኙ ህጋዊ መሆኑን በገዢውም ሆነ በግብር ሰብሳቢው አካል በቀላሉ ለማረጋገጥ ያስችላል።

በተጨማሪም ደረሰኞች በዲጂታል አማራጮች እንደ ኢሜይል እና አጭር የፅሁፍ መልዕክት ለገዢው እንዲደርሱ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ ታትሞ እንዲሰጥም መመሪያው ይፈቅዳል።

መመሪያው በሶፍትዌር አልሚዎች እና አገልግሎት አቅራቢዎች ላይም ጥብቅ የሆኑ መስፈርቶችን አስቀምጧል።

ማንኛውም የሽያጭ መመዝገቢያ ሶፍትዌር አቅራቢ ወይም የክላውድ (Cloud-based SaaS) አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በሚኒስቴሩ እውቅና ማግኘት ይኖርበታል።

ለዚህም እንደ ዋስትና በባንክ ወይም በመድን የተረጋገጠ እስከ 50,000 የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የመልካም አፈፃፀም ዋስትና እንዲያስይዙ ይጠየቃሉ።

ይህም በዘርፉ የሚሰማሩ ድርጅቶች ጥራት ያለውና አስተማማኝ ቴክኖሎጂ ለታክስ ከፋዩ ማቅረባቸውን ለማረጋገጥ የታለመ ነው።

ይፋ የተደረገው አዲስ መመሪያ፣ የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ ሥርዓቱን በበላይነት የሚመሩና የሶፍትዌር ጥራቱን የሚቆጣጠሩ ሁለት ታላላቅ የባለሙያ ስብስቦች እንደሚቋቋሙ ይገልጻል።

በመመሪያው መሠረት፣ የ”ቴክኒክ ቡድን” እና የ”እውቅና ሰጭ ቦርድ” የሚባሉ አካላት የሚቋቋሙ ሲሆን፣ እነዚህ አካላት ማንኛውም በገበያ ላይ የሚውል የሽያጭ መመዝገቢያ ሶፍትዌር የታክስ ሕጉን ማክበሩንና ከመንግስት የመረጃ ቋት ጋር በአግባቡ መገናኘቱን የማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

መመሪያው ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አቅም ለሌላቸው ወይም አዲስ ወደ ንግድ ዓለም ለሚገቡ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ልዩ ድጋፍ የሚያደርግ የ”ክላውድ ሽያጭ መመዝገቢያ ሥርዓትም” (Cloud Sales Register System) ይፋ አድርጓል።

የኢንተርኔት ግንኙነት በማይኖርበት ወቅት ግብይቶች እንዳይስተጓጎሉ የ”ከመስመር ውጭ” (Offline) የሆነ አሰራርም ተዘርግቷል።

በተለይም የምግብ፣ የመጠጥ፣ የመድኃኒት እና መሰል መሰረታዊ የችርቻሮ ንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ታክስ ከፋዮች የኢንተርኔት ግንኙነት ቢቋረጥ እንኳ ግብይቶችን መመዝገብ የሚችሉበትና ግንኙነቱ ሲመለስ መረጃው በራሱ የሚተላለፍበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ተደንግጓል።

የመረጃ ደህንነትን በተመለከተም እያንዳንዱ ሶፍትዌርና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) የደህንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘት እንዳለበት ታዟል።

በተጨማሪም የግል ታክስ ከፋዮች መረጃ ለሶስተኛ ወገን እንዳይጋለጥ እና ለመንግስት የሚተላለፈው መረጃ በሚስጥር (Encryption) የተጠበቀ እንዲሆን ጥብቅ ደንቦች ተቀምጠዋል።

ከኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ መመዝገቢያ ሥርዓት ተስማሚ የሆነ የሽያጭ መመዝገቢያ ስርዓት መጠቀም በሁሉም የሂሳብ መዝገብ በሚይዙ ታክስ ከፋዮች አስገዳጅ ሲሆን ትግበራው ባለስልጣኑ በሚያወጣው መርሐ ግብር መሰረት የሚተገበር ይሆናል ተብሏል።

ይህ አዲስ መመሪያ ሰኔ 2/2018 ዓም በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ በድህረ ገጹ ላይ የተጫነ መሆኑን ታዉቋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እስከ አምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጡ የመረጃ ነጻነት አዋጅ ጸደቀ

ለ15 ዓመታት በስራ ላይ ከቆየው “የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት...

በደቡብ አፍሪካ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተላለፈ ማስጠንቀቂያ

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በሀገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እየተከታተለና...

በበጀት አመቱ 22.9 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው

ከታቀደው 22 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ኩንታል እስካሁን  20...

በቬንዝዌላ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ የ32 ሰዎች ህይወት አልፏል

በቬንዙዌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን 7.2 እና 7.5...