ከበጀቱ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለድህነት ቅነሳና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበው ገንዘብ ነው ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው 5ኛ ዓመት 12ኛ መደበኛ ስብሰባው፤ የከተማዋን የ2019 ዓ.ም ረቂቅ በጀትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በዚህም መሰረት ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚጀምረው የ2019 በጀት ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ በጀት 502.27 ቢሊዮን ብር ሆኖ ወደ ምክር ቤት እንዲመራ መመርያ ሰጥቷል።
ረቂቅ በጀቱ የከተማ አስተዳደሩን የልማት ስትራቴጂዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ድህነትን ለመቀነስ፣ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማረጋገጥ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ተዘርዝሯል።
በተጨማሪም የነዋሪውን የልማት ፍላጎትና የአገልግሎት አቅርቦት ለማሳደግ በተለይም የስራ እድል ፈጠራን ለሚያበረታቱ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማለትም መንገድ፣ ውሃ፣ መኖሪያ ቤት፣ ፅዳት፣ ትራንስፖርትና የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልን ታሳቢ አድርጓል።
ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ሚና ላላቸዉ ዘርፎች ትምህርት፣ ጤና እና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚደረግ ድጎማን ማካተቱን የከንቲባ ጸህፈት ቤት ተናግሯል።
በዚሁ መሰረት ገንዘቡ በከተማው አስተዳደር ለማዕከል ሴክተር ተቋማትና ለክፍለ ከተሞች ለመደበኛና ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያነት ይውላል ይላል።
ከተደለደለው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ወይም 71 በመቶ ለድህነት ቅነሳና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የተመደበ ሲሆን ቀሪው 29 በመቶ ደግሞ ለአስተዳደራዊ ወጪዎች መደልደሉ ተነግሯል።
