በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከ18ሺህ ለሚልቁ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ መሰረተ ልማት ከማሟላት ባለፈ የሚያሰራ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለባለሃብቶች ምቹ ከባቢን ፈጥሯል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ተመራጭ መዳረሻ ሆናለች።
የመደመር መንግሥት በዘርፉ መነቃቃትን ለመፍጠርና አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የአሰራር ማሻሻያና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በፌዴራል ደረጃ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ዶላር በላይ በክልሎች ደግሞ ከ610 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ከ18ሺህ በላይ የሀገር ወስጥና የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አመልክተዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው 17ሺህ 870 ባለሃብቶች በክልሎች እንዲሁም 245ቱ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማሩ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ባለሃብቶቹ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ከ192ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
