|በሪፎርም ሥራው ከ28 ሺህ በላይ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በሰነድም በአድራሻም አልተገኙም ሲሉ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ አስታወቁ።
ከ36 ሺህ 292 መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራትና 19 ዩኒየኖች መሰረዛቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ሺሰማ ከኢፕድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ላለፉት አንድ ዓመት በህብረት ሥራ ማህበራት የሪፎርም ሥራ 28 ሺህ 212 መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በሰነድም ሆነ በአድራሻም አልተገኙም፡፡
ከዚህ በፊት ይህን ያህል ቁጥር እየተባለ ሲነገር የቆየው በስም ደረጃ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ማህበራቱን በሰነድም በአድራሻ ማግኘት ስላልተቻለ ጥሪ ተደርጎላቸው ቢጠየቁም አልተገኙም፡፡
ማህበራቱ ጥሪ ሲደረግላቸው ያለመገኘታቸው ለተዘዋዋሪ ፈንድ ተብሎ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ በነበረ ሂደት የተደራጁ እንደሆኑ ገልጸው፤ ሪፎርሙ መረጃን በማጥራት ማህበራት እንድንቀንስ እድል ሰጥቶናል ብለዋል።
በሪፎርሙ መረጃ የማጥራት ሥራ ተሠርቶ 36 ሺህ 292 መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራትና 19 ዩኒየኖች መሰረዛቸውን የገለጹት አቶ ሺሰማ፤ ምክንያቱም ሕጋዊ ሥርዓት ተከትለው የህብረት ሥራ ማህበራት በራሳቸው ፈርሰው የምስክር ወረቀት መልሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማህበር ሲፈርስ ጥንቃቄ ይፈልጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ የሰበሰበው የሕዝብ ገንዘብ በተወሰኑ ሰዎች አካውንት ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡
የተጠቀሱ ህብረት ሥራ ማህበራት ሥርዓቱን ተከትለው የምስክር ወረቀታቸውን መልሰው በአግባቡ እንዲፈርሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡
አንዱ የሪፎርሙ መነሻ የቁጥራቸውን ያህል ኢኮኖሚያዊ ሚናቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ሺሰማ፤ በአሁኑ ወቅት የቀሩት 89 ሺህ 164 የህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ሪፎርሙ በተጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በውህደት የተፈጠሩ ዓላማ ይዘው ያሉ በርካታ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዳሉም አመልክተዋል፡፡
ጋዜጣ ፕላስ
