የአውሮፓ ሕብረትና የኢትዮጵያ የንግድ ግንኙነትን አዲስ ምዕራፍ ላይ ያደርሳል ተብሎ የሚጠበቀውና ከ500 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ታላቅ የንግድ ፎረም ከ13 ቀናት በኋላ በአዲስ አበባ መካሄድ እንደሚጀምር ተገልጾአል።
አውሮፓ ሕብረት ያዘጋጀውን ይህን ግዙፍ የኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ በር በመጠቀም ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ የንግድና የልማት ትስስሮችን ለመፍጠር ያለመ — “የዓለም አቀፍ በርን አቅም መጠቀም” ወይም በእንግሊዘኛው Unlocking the Global Gateway Potential በሚል መሪ ቃል ከሚያዝያ 12 እስከ 14 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ የአውሮፓና የኢትዮጵያ ግዙፍ ኩባንያዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የፋይናንስ ተቋማት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር እንደገለጹት፣ ይህ ፎረም ሕብረቱና አባል አገራቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በተግባር ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። መድረኩ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶች ትልቅ በር እንደሚከፍትም አምባሳደሯ ገልጸዋል።
በፎረሙ የመጀመሪያ ቀን ሦስት የኢንቨስትመንት ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ይጠበቃል የተባለ ሲሆን፣ በተለይም በዲጂታል ትስስር፣ በመልካም አስተዳደርና በደንብ ማሻሻያ ላይ ትኩረት ያደረገው የዲጂታል ኢኮኖሚ የኢንቨስትመንት ጥቅል በዋናነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ፎረሙ በንጹህ ኃይል ሽግግር፣ በጤና ሥርዓት ግንባታና በዘላቂ የግብርና ምርት እሴት ሰንሰለት ዙሪያ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ሰፊ ውይይት እንደሚያደርግ ታውቋል።
ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ የፓናል ውይይቶችና የንግድ ትስስር መድረኮች የሚካሄዱ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን የመጎብኘት ዕድል እንደሚያገኙም ተገልጿል።
ፎረሙ የአውሮፓ ሕብረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የኢንቨስትመንት ክፍተት ለመሙላት የነደፈው የግሎባል ጌትዌይ ተነሳሽነት አካል መሆኑ ተመላክቷል።
