ለመረጃ ምላሽ የማይሰጡ የስራ ሀላፊዎችን በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርገው የመረጃ ነፃነት አዋጅ

Date:

ረቂቅ ህጉ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ልዩ ጥበቃ የሚሰጥ ፣ የእምባ ጠባቂ ተቋምን ደግሞ አስተዳደራዊ ቅጣትንም በመቅጣት ጭምር ህጉን እንዲያስፈፅም ሙሉ ሀላፊነትን የሰጠው ነው፡፡

የመንግስትን የመረጃ ሚስጥራዊነት ያስቀራል የተባለ እና የግል ድርጅቶችን ጭምር ለተጠየቁት መረጃ ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስገድደው የመረጃ ነፃነት አዋጅ ነው ዛሬ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የቀረበው፡፡

የመረጃ ነፃነት አዋጁ ለመገናኛ ብዙሃን ጥበቃ የሚሰጥ ድንጋጌዎችንም የያዘ ነው፡፡

ከ17 ዓመታት በፊት ፀድቆ ስራ ላይ ከቆየው የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ተገንጥሎ ለብቻው የተሰናዳው የመረጃ ነፃነት አዋጁ የትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤትና ከመንግስት ጋር የገንዘብ ትስስር ያለው የትኛውም የግል ድርጅቶችንም በማንኛውም ሰው መረጃ ሲጠዩቁ መረጃ የመስጠት ግዴታን ጥሎባቸዋል፡፡

መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ የስራ ሀላፊ ወይም የመረጃ ባለሙያ በወንጀል ህጉ ወይም አግባብነት ባለው ሌላ ህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ በረቂቅ አዋጁ አንቀፅ 54 ተደንግጓል፡፡

የተፈለገውን መረጃ መጠየቅ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎችም ሊሆኑ እንደሚችሉም ከረቂቅ ህጉ ተመልክተናል፡፡

የተጠየቀውን መረጃ ደግሞ የመስጠት ግዴታ በተቋማት የስራ ሀላፊዎች ላይ የተጣለ ሲሆን  ሀላፊው በስራ መብዛትና በሌላ ምክንያት መረጃ ለመስጠት ካልቻሉ መረጃ የሚሰጥ የመረጃ ባለሙያ መመደብ እንዳለባቸው አዋጁ ያስገድዳል፡፡

በስራ ላይ በቆየው የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጅ መሰረት አንድ ሰው መረጃ ጠይቆ ምላሽ እስኪያገኝ እስከ 3 ወር ሊጠብቅ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

አዲሱ አዋጅ የአንድ ሰው የጠየቀውን የሰነድ ወይም ሌላ የቃል መረጃ የማግኘተት መብቱ ቢያንስ በ21 ቢበዛ በ35 ቀን ገደብ እንዲፈፀምለት ደንግጓል፡፡

ነባሩ አዋጅ የመረጃ ነፃነትን ለማስፈፀም ሀላፊነት የተሰጠውን የእምባ ጠባቂ ተቋም ሙሉ ሀላነትን የነፈገ ነበር ተብሏል፡፡

በአዲሱ ሕግ መሰረት ግን የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት መረጃ ለመስጠት እንዳንገራገሩ መረጃው ሲደርሰው መረጃ እንዲሰጡ ሀላፊነት በተጣለባቸው የተቋሙ ሀላፊ ወይም የመረጃ ባለሙያው ላይ አስተዳደራዊ እርምጃን እንዲወስድ ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም እምባ ጠባቂ ስልታዊ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል ይላል ለፓርላማው የቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፡፡ 

በሌላ በኩል አዋጁ ለመገናኛ ብዙሃን ጥበቃ የሚሰጡ ድንጋጌዎችንም ይዟል፡፡

በአዋጁ አንቀፅ 55 መሰረት መረጃን በቅን ልቦና ያሰራጨ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ከተጠያቂነት ነፃ እንዲሆን ተደንግጓል፡፡

ጥፋተኛ ተብሎ ለህጋዊና አስተዳደራዊ ቅጣቶች የማይዳረግባቸው የመረጃ ዓይነቶችም በአንቀፅ 55 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ስር ተዘርዝረዋል፡፡

በህጋዊ መንገድ  ከመንግስት አካል ወይም ከግል ድርጅት በተገኘ ሰነድ ውስጥ የተካተቱትን የተዛባ ወይም ሀሰተኛ መረጃ በቅን ልቦና ለህዝብ ይፋ ማድረግ ህጋዊ ተጠያቂነትን አያስከትልም ተብሏል፡፡

በመገናኛ ብዙሃን ሀሰተኛ ወይም የተዛባ መረጃ ስርጭት ተፈፅሟል ተብሎ በሚመለከተው አካል ክስ ከቀረበ እንኳን ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመስጠቱ  በፊት የመገናና ብዙሃን አዘጋጆችም ሆነ ጋዜጠኞችን ወይም ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ሌሎች ሰዎችን ለእስራት መዳረግን ህጉ ይከለክላል፡፡

በተያያዘ የመረጃ ነፃነት ፍጹም ሊገደብ የማይችል እንዳልሆነ በአለም አቀፉ ስምምነቶችም ጭምር በመስፈሩ ተጠይቀው ይፋ የማይደረጉ በአዋጁ ጥበቃ የሚደረግላቸው የመረጃ ዓይነቶችም በረቂቁ ተዘርዝረዋል፡፡

በመሆኑም የመከላከያና የሀገር ደህንነት መረጃን ጨምሮ የተለያዩ የመረጃ ዓይነቶች የማይገለፁ መረጃዎች ተብለው ተፈርጀዋል፡፡

የህግ አስከባሪና የፍርድ ምርመራ ስራ መረጃ ፣ የሶስተኛ ወገን የግል መረጃ ፣ የሶስተኛ ወገን የንግድ መረጃ ፣ በእምነት የተሰጠ የሶስተኛ ወገን መረጃ ፣ የአለም አቀፉ የግንኙነት መረጃ ፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ መረጃ ፣ የመንግስት የስራ ሰነድ ፣ የሙያ ፈተና እና ምልመላ ሂደት በመረጃ እና ሌሎችም በመረጃ ነፃነት ረቂቅ አዋጁ እንደማይካተቱት ሰምተናል፡፡

ሸገር 102.1

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

“ሕገ መንግሥቱ መገንጠልን ይፈቅዳል ፤ ሕዝቡ ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ዋጋ ይከፍላል”

አቶ ፍሬሕይወት ሳሙኤል(የ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖዎች›› መጽሐፍ ደራሲ) ግዮን መጽሔት :-...

ባለሙያ ባልሆኑ ግለሰቦች የሚሰራጭ የተዛባ መረጃ በታካሚዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነዉ

የሳይካትሪስት የሙያ ፈቃድና ሥልጠና የሌላቸው ግለሰቦች በተለያዩ መገናኛ...

የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና የ1.2 ቢሊዮን ዩሮ ስምምነት ሊፈራረሙ ነው

በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ መካከል በሚካሄደው የንግድ ፎረም መክፈቻ...

የአዳዲስ እና የሁለተኛ ዙር መራጮች አቅምና ሚና

ግዮን መጽሔት :- በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የአዳዲስ (ለመጀመሪያ...