‹‹ወጣት ተቀጣሪ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ነው መኾን ያለበት››

Date:

ወንድምነው ንብረት እጅጉ

(የሕብር ኢቲ ድርጅት መሥራችና ባለቤት)

በኢትዮጵያ በርካታ የሰው ኃይልና ሃብት ቢኖርም፣ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ቁጥር አለ፡፡ ይህ ችግር በአንዳች ሥር ነቀል በሆነ የአመለካከት ለውጥ እልባት አግኝቶ፣ ፈጠራና ዕድገት መስፋት አለበት የሚል ጽኑ አቋም ይዘው ከተንቀሳቀሱና ውጤታማ እየሆኑ ከሚገኙ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች አንዱ የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ ወንድምነው ንብረት እጅጉ ናቸው፡፡

ወንድምነው፣ አሁን ላይ ‹‹ሕብር ኢቲ›› የተሰኘ ተቋም መሥርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ እመርታን እያመጡ ካሉ የንግድ ሰዎች አንዱ ለመሆን ችለዋል፡፡ ለመሆኑ ከየትና እንዴት ተነሡ? ድርጅታቸውስ ምን ምን አገልግሎቶችን በመሥጠት ላይ ይገኛል? አጠቃላይ በሀገራችን ለለውጥና ለላቀ የፈጠራ ብቃት መጎልበት እንቅፋት የሆኑን ችግሮችስ እንዴት ያሉ ናቸው? በሚሉት ነጥቦች ዙርያ የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገናል፡፡ እንሆ!    

ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?

ወንድምነው፡- ወንድምነው ንብረት እጅጉ እባላለሁ፡፡ የሕብር ኢቲ ድርጅት መሥራችና ባለቤት ነኝ፡፡ የሕብር ኢቲ ድርጅት ሐሳቡን ከ2013 ጀምሮ በማጥናት ጀምሮ በ2017 ዓ.ም ለመመሥረት ችያለሁ፡፡

ግዮን፡- ከነበርዎት የሥራ ልምድ አንጻር ማንነትዎን ቢያስተዋውቁ?

ወንድምነው፡- የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን የጨረስኩት ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በዚያን ወቅት እኔ ለሰውም ለሀገሩም እንግዳ ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የትኛውም ነገር ላይ ተሳትፎ ማድረግ ያስደስተኛል፡፡ በትምህርት ላይ እያለሁ የወጣት ሊግ ሰብሳቢ ነበርኩ፡፡ የክረምት በጎ አድራጎትም እሰጥ ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ማኅበራዊ ጉዳዮቸ ላይ ያለኝ ተሳትፎ ከፍ ያለ በመሆኑ ዩኒቨሲርቲ ስገባም ለእንዲህ ዓይነት ነገሮች ፈጣን ነበርኩ፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁም በወጣት ሊግ ውስጥ ምክትል ሰብሳቢ ሆኜ ከማገልገሌም በተጨማሪ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ግቢ ጉባዔ በሰብሳቢነትና በተለያዩ አገልግሎቶች  ውስጥ ተሳታፊ ነበርኩ፡፡ በልቤ ደግሞ ሀብታም መሆን የሚል መርህ ነበረኝ፡፡ በዚህም አንድ ሥራ መፍጠር አለብኝ የሚል እቅድ በውስጤ ሰነቅሁ፡፡ በመሆኑም ዳቦ ቤት በጣም አትራፊ እንደሆነ አውቅ ስለነበር ዳቦ ቤት ለመክፈት እቅድ አወጣሁ፡፡ በማቅድበት ጊዜ ግን ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ እኔ በዚያን ወቅት በረሃ እየሄድኩ ነበር የምማረው፤ በርሃ ሄጄ ሰሊጥ አርሜ ገንዘብ እቆጥራለሁ፡፡ ደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ ድንጋይ የሚጭኑ ልጆች ነበሩ፡፡ ከእነርሱ ጋር የተዋወቅኩት በመንፈሳዊ ሕይወት ነው፡፡ እኛ ግቢ ጉባኤ ላይ ሆነን አገልገሎት እንሰጥ ነበር፡፡

በዚያም በመንግሥትም ሆነ በመንፈሳዊ ዘርፍ ያሉ ሰዎች ያውቁኛል፡፡ እነዛን ድንጋይ አውራጆች በዛ መልኩ ስለሚያውቁኝ መታወቂያ እንዲያወጡልኝ አደረኩ፡፡ ከዚያም ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር እንዲያወጡልኝ አደረግኩ፡፡ ተቋሙም98 ሺህ ብር ሰጠኝ፡፡ የቀረውን ብር ከማውቃቸው ሰዎች ሰብስቤ መነሻዬን 138 ሺህ ብር አደረስኩ፡፡ በዚህ ብር 2007 ዓ.ም ላይ የዳቦ ማሽን ገዛሁ፡፡ በዚህ የሥራ ሂደት በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውኛል፡፡ በመጨረሻም ባሕርዳር ከተማ ላይ ዳቦ ቤት ከፍቼ ለማስለመድ ሞከርኩ፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ከብዙ ጥረት በኋላ ከእኔ ዳቦ ይረከብ ጀመር፡፡ የከተማው ሕዝብም ዳቦ ቤቴን በጣም ለምዶ ቀስ በቀስ በሰልፍ ሆነ የሚገዛው፡፡ እኔ ለራሴ ለዩኒቨርሲቲ መመረቂያ የምቸገር ልጅ በዓመት አንድ ግዜ ከቤተሰብ አንድ ሺህ ብር የሚሰጠኝ ሰው የዚህ ሥራ ባለቤት ሆንኩኝ፡፡ በሕይወቴ ከእናትና አባቴ ውጭ ሰው ረድቶኝ አያውቅም፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ 450.50 ብር ከአክስቴ ተቀብያለሁ፡፡ 

በጣም የሚገራርሙ ባለሀብት አጎቶች ነበሩኝ፡፡ እነሱ በእኔ ሕይወት ውስጥ ቦታ ነበራቸው፡፡ እነሱ በሀብታቸው የሚያደርጉትን አይ ነበር፡፡ የሚነዱትን መኪና አውቃለሁ፡፡ እነሱን ስላየሁ በሕይወቴ ተቀጣሪ ሆኜ መኖር ምርጫዬ አልነበረም፡፡ እኔ ከዩኒቨሲርቲ የወጣሁት ራሴን አስመርቄና ቦታ ገዝቼ ነው፡፡ ያ ዳቦ ቤት አሁንም ሥራ ላይ ነው፡፡ ሆቴል ሁሉ ጀምሬ ነበር፤ በኮንስትራክሽን ዘርፉም በተቋራጭነት መንገድና ድልድዮች ሠርቻለሁ፡፡ በርካታ ቤቶችንም ሠርቻለሁ፡፡ ሥራ ብዬ ያልጀመርኩት ነገር የለም፡፡ በእንጀራ መጋገር፣ በእንጨት ሥራና እንዲሁም በብዙ ዓይነት የንግድ ሥራዎች ላይ ተሳትፌያለሁ፡፡

በመንግሥት በኩል ባሉ የተሳትፎ ሥራዎችም ላይ ንቁ ነበርኩ፡፡ በደብረ ታቦር ከተማ ላይ የከተማ አስተዳደር አመራር ሆኜም ስሠራ ነበር፡፡ የእኔ አእምሮ ግን መቀጠር አልነበረም የሚያስበው፡፡ የእኔ አእምሮ የሚያስበው ቢዝነስ መፍጠር ነው፡፡ ሰው በወጣትነቱ የመንግሥት ተቋም ላይ ተቀምጦ መሥራት ከሥራ ፈጣሪነት አንጻር ሀገር እንደማገልገል አይቆጠርም፡፡ ምክንያቱም ወጣት ተቀጣሪ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ ነው መሆን ያለበት፡፡ የመጀመሪያው የፋይናንስ ቁልፍ መሥራትና ቢዝነስ መፍጠር ነው፡፡ የአማራ ክልል የሲቪል አሶሴሽን የፋይናንስ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ሆኜም ሰርቻለሁ፡፡ ድርጅቱን ካቋቋሙና ዋጋ ከከፈሉ ሰዎች ውስጥም አንዱ ነኝ፡፡

ግዮን፡- በኢንጂነሪንግ መቼ ተመረቁ?

ወንድምነው፡- በኢንጂነሪንግ የተመረቅኩበት በ2009 ዓ.ም ነው፡፡ ከተመረቅሁ በኋላ ወደ ንግድ አለሙ ነው የገባሁት፡፡ ተጨማሪ ትምህርት ለመውሰድ እድል አላገኘሁም፡፡ ምክንያቱም በጣም ባተሌ ስለሆንኩ ነው፡፡ ወደፊት ተጨማሪ ትምህርቶችን መማር እችላለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ግን ወጣትነቴን ቢዝነሱ ላይ ማተኮርን እሻለሁ፡፡ ከመንግሥት ተቋም ወጥቼ የተለያዩ ሥልጠናዎች ወስጃለሁ፤ ለሌሎችም ሥልጠና ሰጥቻለሁ፡፡ በማርኬቲንግ ሥራ ውስጥ ሰባት ዓመታት ቆይቻለሁ፡፡

ግዮን፡- የሕብር ኢቲ ድርጅትን ለመመሥረት ምን አነሳሳዎ?

ወንድምነው፡- ሕብር ኢቲን ማጥናት የጀመርኩት እንዳልኩት 2013 ዓ.ም ነው፡፡ ድርጅቱን ለመመሥረት ያነሳሳኝ በውስጤ ያለው የሥራ ፍላጎትና ሁሌም አዲስ ነገር የመሻት ስሜቴ ነው፡፡ እዚህ ሀገር ላይ ሁለት ዓይነት ድህነቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የአስተሳሰብና የእይታ ድህነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቁሳዊ ድህነት ነው፡፡ ሁለቱ ድህነቶች ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን እነዚህ ድህነቶች ስላሉ ሰው በ40 እና በ50 ዓመት እድሜውም የገንዘብ ፍላጎቱን መቅረፍ አልቻለም፡፡ ለምንድነው በዚህ እድሜያችን የገንዘብ ችግራችንን መፍታት ያልቻልነው የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ሀገር ሰው ሥራ እየሠራ ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን ሥራው በቂ አይደለም፤ ወይም በአግባቡ እየተከናወነ አይደለም፡፡ እራስን ማኖር የማያስችል ሥራን እንደሰራ መቁጠር ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ባደጉት ሀገራት እኔም እንዳየሁት እንዳነበብነውም መንገድና መዝናኛዎች በሥራ ሰዓት ጭር ያሉ ጸጥ ያሉ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሰው ሁሉ በተግባር ሥራ ላይ ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ሀገር ግን በሥራ ሰዓትም ሆነ በየትኛውም ጊዜ ሰው ሁሉ መንገድ ላይና መዝናኛዎች ላይ ነው፡፡ በየአደባባዩና በየመንገዱ የሰው ጎርፍ ተበትኖ ነው የሚታየው፡፡ በእርግጥ ሁሉም በየፊናው እየሠራና ለሥራ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሥራው ተግባራዊ ሕይወቱን ከድህነት ሊያላቅቅለት አልቻለም፡፡

ስለዚህ የአደጉ ሀገራት የማደጋቸውና የመምጠቃቸው ምክንያት ምንድነው? ለሚለው የሥራ ባሕላቸው መሆኑን ማየት ያስፈልጋል፡፡ የኛ ሀገር በተፈጥሮ የታደለች ሀገር ናት፡፡ የሰው ሀብት አላት፤ ይህን ሁሉ ሀብት ይዛ ለምንድነው የደኸየነው? ምክንያቱም ትንሽ ሀገር ሆነው የካበተ የተፈጥሮ ሀብት ያላቸው ሀገሮች አድገው አይተናል፡፡ የእኛ ሀገር አለማደጓ ግን በጣም ያማል፡፡ እንደ ዱባይ፤ ቻይና እንዲሁም አሜሪካ ያሉ የሰባና ሰማኒያ ዓመት የእድገት እድሜ ያላቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ ዱባይ እና ቻይና በ40 ዓመት ውስጥ ነው ያደጉት፡፡ ሲንጋፖርም እንዲሁ ነች፡፡ እነዚህን ሀገራት ስናይ ኢትዮጵያ ለምን እንዳልተነሳች የሚገባን ነገር አለ፡፡ ምክንያቱም በተፈጥሮ ሀብትና በሰው ኃይል ከብቁ በላይ ነን፡፡ ስለዚህ ክፍተቱ ያለው ሌላ ቦታ ነው፡፡ ይህ ክፍተት በእኔ እይታ በሁለት መንገድ የመጣ ነው፡፡ በመጀመሪያ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ላይ ትልቁ በሽታ ነው፡፡ በሀገራችን ፓራዳይም ሺፍት ያስፈልጋል፡፡ የትምህርት ሥርዓታችን እራሱ አስተሳሰብ ለውጥ ላይ መሥራት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ሰዎች ከሦስት ነገር ማለትም ከአካባቢያቸው፣ ከሚያዩትና ከሚውሉበት አይወጡም፡፡

በቀላል ምሳሌ ብንገልው ለስራ ትጉህ ከሆነ ሰው ጋር የሚውል ሰው ለስራ ትጉህ ይሆናል፤ ከሰነፍ ጋር የሚውልም ሰው እንደዛው ሰነፍ ይሆናል፡፡ ከአስር ባለሀብት ጋር የዋለ አንድ ድሃ 11ኛው ባለሀብት እሱ ይሆናል፤ ከአስር ድሃ ጋር የዋለ አንድ ሀብታም 11ኛው ድሃ እሱ ይሆናል፡፡ የሚሰሙትና የሚያዩትም ሁሉ ያንኑ ውሏቸውን ይመስላሉ፡፡ ከዚህም ነው ሰው በሰውነቱ ሳይለያይ በቋንቋ የሚለያየው፡፡ ሰዎች ከሚሰሙትና ከሚያዩት ውጭ ተጨማሪ ነገር ሊያመጡ አይችሉም፡፡ በሀገራችን ታታሪ የሆኑ ሰዎች ትንሽ ናቸው፡፡ የእነዚህን የታታሪ ሰዎች ሐሳብ የሚቀበሉ ሰዎች ደግሞ የሉም፡፡ ጥሩ ነገር ይዞ የቀረበን ሰው ሲያዩ የሚሆንለት እራሱ አይመስላቸውም፡፡ እንደውም እንቅፋት ይሆኑበታል፡፡ ጠንካራ የሚባሉ ሰዎች በሰነፍ ሰዎች ይዋጣሉ፡፡ ማበረታቻና ክብር አይሰጣቸውም፡፡ የሚሠሩ ሰዎች ክብር ቢሰጣቸው የማይሠሩ ሰዎችም ክብር ለማግኘት ወደ ሥራ እየተጉ ይሄዳሉ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ሀገር ታድጋለች፡፡

በመጀመሪያ ግለሰብ መለወጥ ሲጀምር ብዙዎች የለውጡ አካል እየሆኑ ይመጣሉ፡፡ ይህ ሲሆን ሀገርም ትለወጣለች፡፡ ለውጥ ከብዙኃን አይጀምርም፤ ለውጥ የሚጀምረው ከግለሰብና ከጥቂቶች ነው፡፡ የሰው ልጅም ከአንድ ጀምሮ ነው እዚህ ቁጥር ላይ የደረሰው፡፡ ስለዚህ ለውጥ ሲመጣ መደገፍና ማገዝ አልፎም የለውጥ አካላነትን መላበስ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ እይታችን መስተካከል ይኖርበታል፡፡ ሀገራችን መሥራት ያለባት የእይታ ለውጥ ላይ ነው፡፡ ይህች ሀገር መሠልጠን አለባት፡፡ ትውልዱ ካልሠለጠነ ሀገሪቱን ማልማት አይችልም፡፡ ባልሠለጠነ ትውልድ ሀገር ሊለማ አይችልም፤ ቢለማም መልሶ ይጠፋል፡፡ ሀገር ለምቶ መልሶ የሚጠፋው በአስተሳሰብ ችግር ነው፡፡

ግዮን፡- የሕብር ኢቲ የስልጠና ተቋም በውስጡ ተጨማሪ ምን ምን ነገሮች አሉት?

ወንድምነው፡- የእኛ ተቋም አራት ፈርጆች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ማሠልጠንና ሕብረት መፍጠር ነው፡፡ አሠልጥነን አንለቀውም፤ እንይዘዋለን፡፡ ሕብረት መፍጠሩ አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡ ከግለሰብ ድርጅት እንደሚልቀው ሁሉ ከአንድ ሰው ብዙ ሰዎች ውል ያለው ተግባር መፈጸም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሕብር ኢቲ ከያዛቸው አራት መሠረታዊ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሥልጠና ነው፡፡ ድርጅታችን ፈጠራ፤ፋይናንስና ቴክኖሎጂ ላይ ስልጠናዎችን በሰፊው ለመስጠት ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ነው፤ በመስጠትም ላይ እንገኛለን፡፡ 

ከሕብር ኢቲ ሥልጠና ተቋም ውጭ ሌሎች ሦስት ዘርፎች አሉን፡፡ እነርሱም የሕብር ኢቲ ብድርና ቁጠባ፣ የሕብር ኢቲ ኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲሁም የሕብር ኢቲ ዲጂታል እቁብ ናቸው፡፡ የሕብር ኢቲ ዓላማ የሥራ እድሎችን መስጠት ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ቅጥር ይሰጣል፡፡ የኮሚሽን ሠራተኞች በነፃነት እንዲሠሩ እድል ይሰጣል፡፡ ማንም ሰው አስተዋውቆ ኮሚሽን እንዲከፈለው ያደርጋል፡፡ እነዚህ የኮሚሽን ሙያተኞች እኛው ጋር ይቀጠራሉ፡፡ እንዲቆጥቡና ብድር ወስደው የራሳቸውን ቁሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ይደረጋል፡፡ አባላቱ እቁብ እንዲጥሉም ይደረጋል፡፡ ሕብር ኢቲ ተቋም በቴክኖሎጂ የሚመራ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የድርጅታችን ማንኛውንም ነገር ባለበት ቦታ ሆኖ መከታተል ይችላል፡፡

ግዮን፡- የአሠልጣኞቻችሁ ደረጃ ምን ላይ የሚገኝ ነው?

ወንድምነው፡- ሥልጠና ላይ እኔ ለረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን ስወስድም ስሰጥም ቆይቻለሁ፡፡ አሠልጣኞች ከእኛ እውቀት የላቀ እውቀት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ፕሮፌሽናል አሠልጣኞች በቅጥርም ሆነ በግዜያዊነት አምጥተን እንዲያሠለጥኑ እናደርጋለን፡፡ ድርጅታችን በተለያዩ ዘርፎች አሠልጣኖችን በማምጣት ያሠለጥናል፡፡ ሥልጠናውንም የሚሰጥበት የራሱ ፓኬጅ አለው፡፡

ግዮን፡- ሕብር ኢቲ የተባለበት ምክንያት ምንድነው?

ወንድምነው፡- ሕብር የሚለው ስያሜ አንድነትና ሕብረትን የሚጠቁም ነው፡፡ ሕብር ማለት ሁለት ዓይነት ትርጓሜ አለው፡፡ የመጀመሪያው ሕብረት አንድነትና ጥምረት ማለት ነው፡፡ በሌላ  በኩል ደግሞ ድርጅታችንን ሕብር ያልነው በርካታ አገልግሎት በአንድ ተቋም ሥር ያቀረበ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ሕብር እቁብ፣ ሕብር ብድርና ቁጠባ፣ ሕብር ሥልጠና፣ ሕብር ኢንቨስትመንት ሁሉም በአንድ ሕብር ሥር የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች አካተን ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻርም ሁሉንም የሰው ዘር አቀናጅተን የምንሠራ በመሆኑ ሕብር ብለነዋል፡፡ ድርጅታችን ከሕብር ጋር የሚሠራ ሁሉን ያገለግላል፤ ይገለገላል፤ አብሮ ያድጋል፤ ሕብር የሚለውን ስያሜ የሰጠነው በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ሕብር ስለሚያስፈልጋትም ጭምር ነው፡፡ የሕብረትን አንድነት ከስሙ ጀምረን እናሳይ በሚል ነው ሕብር ያልነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ላይ ያለንን ክህሎት አውጥተን በሕብረት እንሥራ የሚል ትርጓሜ ያለው ስም ነው የሰጠነው፡፡

ግዮን፡- ሕብር ኢቲ ከሌሎች ብድርና ቁጠባ ተቋማት በምን ይለያል?

ወንድምነው፡- የእኛ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከሌላው የሚለየው ስለቢዝነስ ያወቀና የሰለጠነ የሰው ኃይል በዙሪያው መኖሩ ነው፡፡ ስለአስተሳሰብ ለውጥና ስለአመራር በቂ ግንዛቤ ያለው ስለፋይናንስ አያያዝ ሥራ ፈጠራ ያወቀ ሰው ነው በእኛ ተቋም ዙሪያ ያለው፡፡ ሕብር ኢቲ ብድር ነው የሚሰጠው፤ ብድር ሲሰጥ ዕውቀት ከሌለ ተመልሶ ይጠፋል፡፡ ከሁሉም በፊት ማይንድ ሴት ይቀድማል፡፡ዕውቀትን ሀብት ካደረጉ በኋላ ወደ ብድር መሄድ ይቻላል፡፡ ሰዎችን ስለፋይናንስ አያያዝና ሥራ ፈጣሪነት ላይ በደንብ ካሠለጠንን በኋላ ነው ብድር የምንሰጠው፡፡ ይሄ የእኛን ብድርና ቁጠባ ተቋም ከሌላው የተለየ ያደርገዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ተቋሙ ራሱ የሠልጣኞች ነው፡፡ የተቋሙ ባለቤቶች እራሳቸው ተበዳሪዎች ባለአክስዮን የሆኑበት ነው፡፡ ይሄ በራሱ ከሌሎች መሰል ተቋማት ልዩ ያደርገዋል፡፡ እኛ ብድር ከመስጠታችን በፊት ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ይህን የምናደርገው ሠልጣኙ በዕውቀትና  በተገቢው መንገድ የሚያደርገውን ስለሚረዳ  ክስረትና የኋልዮሽ ጉዞ ከተበዳሪው የራቁ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡

ግዮን፡- የሕብር ኢቲ ቅርንጫፎች የት የት ይገኛሉ?

ወንድምነው፡- ዋና መሥሪያ ቤታችን አዲስ አበባ መገናኛ ሲቲ ሞል 11ኛ ፎቅ ላይ ይገኛል፡፡ ቅርንጫፍ ቢሯችን ሐዋሳ እና ባህርዳር ነው የሚገኙት፡፡ እዚያም በርካታ በዘርፉ በዕውቀት የበቁ አጋሮች አሉን፡፡ በቅርቡ ደግሞ መቀሌ፤ድሬዳዋ እና ሌሎች ከተሞች ላይ እንከፍታለን፡፡

ግዮን፡- ስለ ሥራችሁ ሕዝቡ ያለው ተቀባይነት ምን ይመስላል?

ቀጣዩንና የመጨረሻው ክፍል አርብ ጥቅምት 21- 2018 ዓ.ም ይጠብቁ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...