“ኢትዮጵያ የኒኩሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ቁርጠኛ ናት”
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ፤ ኢትዮጵያ ለሁሉን አቀፍ ዕድገት የኒኩሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ቁርጠኛ ናት አሉ።
በኦስትርያ ቬና እየተካሄደ በሚገኘው 69ኛው የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር በለጠ ሞላ፤ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ለሆነ ሀገራዊ እድገት ያግዛት ዘንድ የኒኩሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ አላማ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕዳሴ ግድብን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ይፋ ካደረጓቸዉ ፕሮጀክቶች መካከል የኒኩሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ማዋል መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ኤጀንሲው ፕሮጀክቱን እንዲያግዝ ጥሪ ማቅረባቸውን ኤፍኤምሲ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የኒዉክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ማለትም ለሀይል አቅርቦት፣ ለምርምር፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለአካባቢ ጥበቃ መጠቀም ያስችላት ዘንድ በፈረንጆቹ ከ1957 ጀምሮ የኤጀንሲው አባል መሆኗ ይታወቃል።
