የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ፀሐፊ ኤርትራና ኢትዮጵያ ከ25 ዓመታት በፊት በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን ግጭት በይፋ ያቆመውን ስምምነት ዳግም እንዲያከብሩ አሳሰቡ። የታደሱ ውጥረቶች የክልሉን ሰላም ሊያደፈርሱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት፣ “ዛሬ የአልጀርስ ስምምነት የተፈረመበት 25ኛ ዓመት ነው። ይህ ስምምነት በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን የድንበር ግጭት በይፋ ያቆመ እና በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር ወሳኝ ማዕቀፍ ያስቀመጠ ታሪካዊ የሰላም ውል ነው” ብለዋል።
መግለጫው፣ ስምምነቱ “የጋራ ድንበሩን ለመወሰን የሚያስችሉ አሠራሮችን” ለመፍጠር እንደረዳ ከጠቆመ በኋላ፣ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ፣ “ለሁለቱም አገሮች የሉዓላዊነት እና የክልል አንድነት መሰረታዊ መርሆችንም አረጋግጧል” ብሏል።
“በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ፣ ዋና ፀሐፊው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአልጀርስ ስምምነት ያለውን ጽኑ ድጋፍ በድጋሚ ይገልጻሉ።” መግለጫው አክሎም “ከሰባት ዓመታት በፊት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በጋራ መግለጫ አማካይነት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት አድሰዋል፤ ይህም የውይይትና የትብብርን ኃይል የሚያሳይ ነው” ብሏል።
ውጥረቶች እንደገና በታዩበት በዚህ ወቅት፣ ጉቴሬዝ “ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በአልጀርስ ስምምነት የተካተቱትን ዘላቂ ሰላም፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ራዕይ ዳግም እንዲያከብሩ እና የመልካም ጉርብትና ግንኙነት ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያጠናክሩ” አሳስበዋል።
የተመድ ዋና ፀሐፊው በተጨማሪም ሁለቱም ወገኖች “የልማት ትብብርን ለማራመድ ከክልላዊና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር መስራታቸውን እንዲቀጥሉ” ጥሪ አቅርበዋል።
ኤርትራ እና ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ.1998-2000 ዓ.ም. በተደረገውና በሁለቱም ወገን እስከ 80,000 የሚደርሱ ሰዎች ለሞት በተዳረጉበት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የአልጀርስ ስምምነትን መፈራረማቸው ይታወሳል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከጊዜ በኋላ ዓለም አቀፍ የድንበር ኮሚሽን በግጭቱ መነሻ ነጥብ የነበረችው ባድመ የኤርትራ እንደሆነች ወስኗል፤ በሌላ በኩል ኤርትራ በአሰብ ወደብ የያዘችውን ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ጭነት ለማካካስ ለኢትዮጵያ ካሳ እንድትከፍል ወስኖ ነበር።
