- ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም
የትግራይ ሕዝብ ሀገሩን ከሚወጉት ጋር ተሰልፎ የመዋጋት ጥቁር ታሪክ የለውም ሲሉ የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬርያ ኢብራሂም ገለጹ፡፡
የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬርያ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሕወሓት ቡድን ግን የተሰለፈው ከትግራይ ሕዝብና ከሀገሪቱ ጠላት ጋር ነው።
የትግራይ ሕዝብ ሀገሩን የሚወድ እንጅ ከሕዝብና ከሀገሩ ጋር ተቃራኒ ሆኖ የሚሰለፍበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም፤ እንደዚህ ዓይነት ታሪክም የለውም ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ ኬርያ ገለጻ፤ የትግራይ ሕዝብና የትግራይ ምድር የጦር ሜዳ እንዳይሆን ህዝቡ ሊጠነቀቅ ይባል፡፡
ይህ እንዳይከሰት አሰላለፋችንን ማስተካከል እና ከጥፋት ኃይሎች በተቃራኒ መቆም አለብን ሲሉ መክረዋል።
ለትግራይ ሕዝብ ሲባል የጦርነት በር መዘጋት አለበት ያሉት ወይዘሮ ኬርያ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ለሰላም ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የትግራይ ሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው ከፌዴራል መንግሥት ጎን በመሰለፍ በሰላማዊ እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንጅ በጦርነት አይፈታም ሲሉም አስረድተዋል።
