የኢትዮጵያን የ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮቦንድ ዕዳ የገዙ የግል አበዳሪዎች ቡድን፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በለንደን ፍርድ ቤት የሕግ እርምጃ ለመውሰድ መወሰናቸውን አስታዉቀዋል።
አበዳሪዎቹ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት፣ በኢትዮጵያ እና በግል አበዳሪዎቹ መካከል ተደርሶ የነበረው የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት በይፋዊ አበዳሪዎች ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ነው።
እንደ ፈረንሳይ እና ቻይና ያሉ ሀገራትን ያቀፈው የኢትዮጵያ ይፋዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ እና በግል አበዳሪዎች መካከል ተደርሶ የነበረውን የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ውድቅ አድርገውታል። ኮሚቴው ስምምነቱን ውድቅ ያደረገው “አበዳሪዎቹ ያደረጉት የዕዳ ቅነሳ ጥረት እጅግ አነስተኛ ነው” በሚል ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
ይህንን ተከትሎ በቪአር ካፒታል እና ፋራሎን ካፒታል ማኔጅመንት የሚመራው የግል አበዳሪዎች ኮሚቴ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ የይፋዊ አበዳሪዎቹ ውሳኔ “ምክንያታዊ ያልሆነ” ነው ብሎታል።
ኮሚቴው አክሎም “በአበዳሪዎች ኮሚቴው ውሳኔ ምክንያት አዋጭ የሆነ የቀጣይ መንገድ ባለመኖሩ፣ ያልተከፈለውን ዋና ዕዳ እና ወለድ ለማስከፈል በእንግሊዝ ፍርድ ቤት የሕግ እርምጃ ከመውሰድ ውጭ ሌላ አማራጭ አልተሰጠንም” ብሏል።
የዕዳ ፍትሃዊነትን የሚሟገተውና መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው “Debt Justice” የተባለው ድርጅት፣ ይፋዊ አበዳሪዎች ስምምነቱን ውድቅ ማድረጋቸውን ደግፏል።
ድርጅቱ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የግል አበዳሪዎቹ የፈለጉት ስምምነት ቢጸድቅ ኖሮ፣ ከመንግሥታት አበዳሪዎች በ28 በመቶ የበለጠ ክፍያ ከኢትዮጵያ ያገኙ ነበር።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሄይዲ ቾው በሰጡት ምላሽ “ይፋዊ አበዳሪዎች ስምምነቱን ውድቅ በማድረጋቸው ትክክል ናቸው። ይህ ስምምነት ቢጸድቅ ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአቅሙ በላይ ከፍተኛ ክፍያ እንዲከፍል በማስገደድ፣ እንደ ጤና እና ትምህርት ያሉ መሠረታዊ የሕዝብ አገልግሎቶችን አደጋ ላይ ይጥል ነበር” ብለዋል።
የግል አበዳሪዎች ክሳቸውን የሚያቀርቡት በለንደን ፍርድ ቤት በመሆኑ፣ ዳይሬክተሯ የእንግሊዝ መንግሥት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ፓርላማ ቀርቦ የሚገኘው የዕዳ እፎይታ ረቂቅ አዋጅ እንዲጸድቅ ተጠይቋል።
ይህ አዋጅ የግል አበዳሪዎች የዕዳ ሽግሽግ ድርድር በሚካሄድበት ወቅት ክስ እንዳይመሰርቱና ከሌሎች አበዳሪዎች በላይ ክፍያ እንዳይጠይቁ የሚከለክል ሕግ መሆኑ ይታወቃል።
