የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል፣ መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው “ዘ ሴንትሪ” የተሠኘው መንግሥታዊ ያልኾነ ተቋም በኤርትራ ላይ ያወጣው ሪፖርት “የስም ማጥፋት ውንጀላ” ነው በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት ጽሁፍ ውድቅ አድርገዋል።
የማነ፣ የተወሰኑ የተቋሙ የቦርድ አባላት፣ “በአደራዳሪነት ሽፋን የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነትን በማባባስ” የሚታወቁ፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት ወግነው የነበሩና የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ነበሩ በማለት ወቅሰዋል።
ተቋሙ “ሥልጣና እ ዝርፊያ፤ የኤርትራ ጦር ጣልቃ ገብነት በትግራይ‘’ በሚል ርዕስ ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ ኤርትራ ሠራዊቷን እንደገና እያስታጠቀችና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቿም በትግራይ በሰዎች ዝውውር፣ በሰዎች እገታና በሕገወጥ የወርቅ ማዕድን ንግድ እንደሚሳተፉ ገልጦ ነበር። [ዋዜማ]
