በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ እየተዘጋጀ ያለው አእላፋት ሳምንት የጃን ፎረም መድረክ ላይ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችና የንግድ ሥራ ጀማሪ ወጣቶች የተገኙበት የኦርቶዶክሳውያን ነጋዴዎች ትሥሥር መድረክ (Orthodox Business Networking Event) ተከናውኗል።
“በንግሥት ህንደኬ በገንዘብዋ ሁሉ የሠለጠነ ነበረ” በሚለው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ፍልስፍና ላይ በተመሠረተውና የቢዝነስ ዘርፍ ላይ በሚሠራው ጃን ህንደኬ አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ “ኦርቶዶክሳዊ የንግድ እሳቤ’ የሚል የመነሻ ጽሑፍ በአቶ ብንያም አሕመድ ለታዳሚያን ቀርቦ ጥልቅና ገንቢ ውይይት ተደርጎበታል።
በዕለቱ በተከናወነው የፓናል ውይይት ላይም የሥራ ልምዳቸውን ያካፈሉት ወ/ሮ ማራኪ ተጠምቀ የማኪ ኢንቲሪየር ዲዛይን ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፣ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም ዳግማዊ የርግብ ጋርመንት ፖርትነር እና አቶ ልዑል ደረጀ የማርኬቲንግና ሪል ስቴት ባለሙያ የንግድ ሥራን ምንነትና ተግዳሮቶች እንደ ክርስቲያንም በንግድ ሥራ ላይ መከተል ሰለሚገባ አካሄድ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ታዳሚዎችም የመድረኩን መጀመር አወድሰው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የንግድ ትሥሥሩ ለወጣት የንግድ አሳብ ባለቤቶች ልምድና አቅም ካላቸው ኦርቶዶክሳውያን ጋር ከማገናኘት ባለፈ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ያለውን የላቀ ፋይዳ አንስተዋል።
በመድረኩ የተገኙ ከዐሥር በላይ የንግድ ተቋማትም ለኦርቶዶክሳውያን ተጠቃሚዎች የልደት በዓልን ተንተርሶ የተለያዩ ቅናሾች ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል። ኦርቶዶክሳዊው የንግድ ትሥሥር መድረክ በጃን ህንደኬ አዘጋጅነት በቋሚነት እንደሚካሔድ ተገልጾአል::
