በአማራ ክልል ያለው እገታና የመንገድ ደኀንነች ሁኔታ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ አስቸጋሪ መሆኑን የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።
በእገታ፣ በትራፊኮችና በፓርኪንግ ዙሪያ ከፈጥኖ ደራሽ ኮሚሽነሮች፣ ከሚመለከታው የጸጥታ አካላት ሁሉ እየተነጋገሩ መሆኑን የገለጹት አንድ የማኅበሩ አመራር፣ በኦሮሚያ ክልል ክስተቶቹ በተወሰነ መልኩ ቀንሰው ተመልሰው እንደሚስተዋሉ ገልጸው፣ ” በአማራ ክልል ያለው እገታ ከቁጥጥራችን ውጪ ነው፤ ለማን እንደምናመለከትም አናውቅም ” ብለዋል።
በአማራ ክልል ከእገታ ጋር በተያያዘ በርካታ ሹፌሮች ወደ ማኀበሩ በየጊዜው እንደሚደውሉ ተናግረው፣ ” ለምሳሌ በጎንደር በኩል ማዳበሪያና ነዳጅ የጫኑ አሽከርካሪዎች በእጀባ ካልሆነ በስተቀር በግል ደረጃ መንቀሳቀስ አልቻሉም ” ሲሉ ነግረውናል።
ሰሞኑንም በደጀን በኩል በርካታ ሹፌሮች ” አታልፉም ” ተብለው መንገድ ላይ እንደቆሙ ገልጸው፣ ” መንገድ ተከፈተ ሲባል ደግሞ አደጋ አለ። አማራ ክልል ያለው ነገር ከኛ አቅም በላይ ነው፤ እዛ አካባቢ ያለው የሰላም ሁኔታ እስካልተፈታ ድረስ ጉዳዩ አይቀልም ” ነው ያሉት።
አመራሩ፣ በኦሮሚያ ክልል ድርጊቱ እየቀነሰ የመጣው በማኅበሩ ተፅዕኖና በመንግስት ፍላጎት መሆኑን በመጥቀስ፣ ” እየቀነሰ መጣ እንጅ ብቅ ጥልቀቅ እያለ ሾፌሮቻችን አደጋ ላይ መውደቃቸው አልቀረም፡፡ አሁን በጣም ያሰጋል፤ ሾፌሮች በተለያዩ ነገሮች ምሬት ውስጥ ናቸው፤ የመንገድ ችግር አለ፤ ሾፌርን ማንም ዱርዬ ነው በጥፊ የሚመታው፤ ጥበቃ ነኝ በሚል ሚሊሻ ነው የሚዘረፈው ” ብለዋል፡፡
ሰሞኑንም በድሬዳዋ መስመር ሹፌሮች እንደታገቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ” የመኪናውን ሁለት ጎማዎች በጥይት መቱት፣ አንዱ ሾፌር ተደበቃቸው፣ ሁለቱን ወሰዷቸው፡፡ ግን እዛው በቅርብ ርቀት የፌደራል ፖሊስ እንዳለ ነው የነገረኝ ” ሲሉ ከእገታ ያመለጠው ሹፌር መናገሩን ገልጸዋል፡፡
” አሽከርካሪዎቻችን በምሽት ባይንቀሳቀሱ ነው የምንመክረው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ችግር ስለላ ይህንን ከግምት ውስጥ አስገብተው ለሀገር ኢኮኖሚ የሚደክሙት አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ አድርገው መንቀሳቀስ አለባቸው ” ብለዋል፡፡
” እንደ ማህብረሰብና እንደ መንግስት ደግሞ የጥንቃቄ ጥበቃ እንዲደረግልን እንፈልጋለን፡፡ ስጋቶች አሉባቸው በሚባሉ ቦታዎችም በጥንቃቄና በትኩረት ክትትል ይደረግ ” ሲሉም ጠይቀዋል።
” አሽከርካሪዎች ወደ ሥራ ማቆም ከሄዱ ልንቆጣጠረው አንችልም፤ እንደ ማኅበር ስጋታችን ይሄ ነው፤ ሥራ ወደ ማቆም ከተኬደ መመለስ አንችልም፤ የአሽከርካሪዎችም ቀጣሪዎቻቸው ብዙ ስለሆኑ ከየአቅጣጫው መጥራት ይከብዳል፤ አንድ ጊዜ ቁልፋቸውን ቁጭ ካደረጉ የሚፈጠረው ከባድ ሁኔታ ነው ” በማለት አስገንዝበዋል፡፡
የሹፌሮችን ውሎ በየቀኑ በመከታታል ታማኝ መረጃ የሚያቀርበው ” የሾፌሮች እንደበት ” ሰሞኑን ባጋራው መረጃ መሠረት፣ በአንድ ወር ውስጥ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከ14 በላይ ሹፌሮች መታገታቸውን አስታውቋል፡፡
ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ እስከዛሬ ታገቱ ከሚባሉት ሹፌሮች ምን ያህሉ እንደተለቀቁና እንዳልተለቀቁ፣ ምን ያህል እንደተገደሉ የሚያስረዳ ሪፖርት አዘጋጅቶ እንደሆን የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበርን የጠየቀ ሲሆን፣ ማኅበሩም አንዱ ፈታኝ የሆነበት ጉዳይ መረጃዎችን ማሰባሰብ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ምክንያቱን ሲያስረዳም፣ ሾፌሮች እንደታገቱ መረጃ ከደረሳቸው በኋላ ስለመለቀቃቸው መረጃ ማግኘት እንደሚያስቸግር፣ አጋቾች አድራሻቸውን ስለሚቀበሏቸውና ዳግሞ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ስለሚሰጉ ታግተው የሚለቀቁ ሹፌሮችም የሚሰጡት መረጃ እንደሌለ ገልጾ፣ ” ስለዚህ ዳታ መሰብሰቡ ችግር ነው ” ብሏል።
እገታና ግድያ የሚስተዋልባቸው ቦታዎች በመንግስት በኩል ጥብቅ ጥበቃ ማድረግ፣ ” የወረዳ ታጣቂዎች አካላት ከአጋቾች ጋር እየሰሩ ነው ” የሚል ስጋት ስላለ እነርሱንም የጥበቃው አካል ማድረግ፣ አሽከርካሪዎች ከቀኑ 10 ወዲያ በምሽት ከማሽከርከር መታቀብ የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን ጠቁሟል።
@tikvahethiopia
