ኬኒያዊዉ አክቲቪስት ቦኒፌስ ምዋንጊ፤ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በኬኒያ መንግስትን ተቃዉመዉ ሰልፍ የወጡትን ዜጎች አነሳስቷል በሚል በሽብርተኝነት መያዙ ተገልጿል፡፡
በዚህ የተቃዉሞ ሰልፍ 19 ሰዎች ህይወታቸዉን ማጣታቸዉ ይታወሳል፡፡
‹‹በኢኮኖሚ ችግርና በመንግስት ተጠያቂነት እጦት የተነሳ ተፈጠረ››በተባለዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ የሽብር ተግባራትን አመቻችቷል በማለት ነዉ ፖሊስ አክቲቪስቱን መክሰሱን የገለጸዉ፡፡
የከተማዋ ፖሊስ በተቃዉሞ ወቅት በጥቅም ላይ ያልዋሉ የአስለቃሽ ጭስና የጦር መሳሪያዎችን ሰልፈኞቹን አስታጥቆም ነበር ብሏል፡፡
የህግ ምሁራን ምዋንጊ ከሽብርተኝነት በተጨማሪ፤ ህገ-ወጥ ጥይቶችን በመያዝ ጭምር ክስ ሊመሰረትበት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ፖሊስ እንደ ላፕቶፕ፣ስልክና ማስታወሻ ደብተር ከቢሮዉ እና ከመኖሪያ ቤቱ መዉረሱን አስታዉቋል፡፡
ብዙዎች ክሱ በመንግስት ላይ የሚደረግ ትችትን ለመግታትና የኬንያ ከፍተኛ ተቺዎችን ዝም ለማሰኘት የሚደረግ ሙከራ ነዉ ብለዋል።
ምዋንጊ በኬኒያ ዉስጥ የረዥም ጊዜ ታጋይና የሲቪል ማህበረሰብ አንቂ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት ሙስናን በመቃወም ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም የፖሊስ አባላት በሚያደርሱት ጭካኔያዊ ተግባር እንዲሁም ባለስልጣናት በሚፈጽሙት የህግ ጥሰት የተነሳ ተጠያቂ የሚያደርጋቸዉ የለም በሚለዉ አቋሙ ለዛቻዎች፤ ማስፈራሪያዎችና እስሮች መዳረጉን የአፍሪካ ኒዉስ ዘገባ ያመላክታል፡፡
