የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ፤ በአገራችን ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከ50 በመቶ በላይ ሴቶች በየዘርፉ በሚካሄዱ የልማት ስራዎች በመሳተፍ የድርሻቸውን እንዳይወጡ ከሚገኘውም የልማት ትሩፋት እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ተግዳሮት እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ለማስቆም የሚረዳ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ እየተካሔደ ነው።
በኢትዮጵያ ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች እና ህጻናት ላይ አካላዊ ጉዳት እና የከፋ የጤና እክል በማድረስ፣ ለውስብስብና ድርብርብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚዳርግ መሆናኑ ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላም በተጎጂዎች ስነልቦና ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠበሳ በቀላሉ የሚሽር ባለመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊከላከለው እንደሚገባ አመላክተዋል።
ጾታዊ ጥቃት ከግለሰብ ጀምሮ በማህበረሰብና በሀገር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በመረዳት ለሴቶችና ህጻናት ሰብዓዊ መብት መከበር የሚረዱ አለም አቀፍ ስምምነቶችን ከማጽደቅ ባሻገር አላሰራ ያሉ ህጎችን የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሀገራችን ለ20ኛ ጊዜ “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ!!” በሚል መሪ ቃል ከነገ ህዳር 16 እስከ ታህሳስ 01/2018 ዓ/ም ድረስ በንቅናቄ በሚከበረው መርሃ ግብር ለ55 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ አማራጮች ግንዛቤ ለመፍጠር መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡
በንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ ስትራቴጂ እና የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ ከማድረግም ባሻገር ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
(መናኸሪያ ሬዲዮ)
