♦️በጸሎት፣በፍቅርና በእምነት እጆች የተገነባችውና መንፈሳዊ መጠለያ የሆነችው የካናዳ ትንሿ ቤተክርስቲያን
✍️✍️በጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ(ሀትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል)ከካናዳ ቶሮንቶ
♦️15 ሌሊት ቀናትች በካናዳ…ይቀጥላል…
የካናዳ ምድርን ከረገጥኩ ነገ(ረቡዕ)ድፍን 15 ቀኔ፤ካናዳን ከአራት አምስቴ በላይ ተመላልሼ ባያትም በውስጧ የያዘቻቸው ምስጢሮችና ታሪኮች እንደአሁኑ ተገልፀውልኝ አያውቁም፤ብዙ ሥፍራዎችን ጎብኝቻለሁ፣ብዙ ውብና ታሪካዊ ቦታዎቿንም አይኖቼ አይተዋል፣ጆሮዎቼም ሠምተዋል፤ ነገር ግን እንደዚህ ነፍሴን ሐሴት ያደረገና የማረከ፣በልቤ ውስጥ የማይረሳ የታሪክ ሐውልት ያቆመ ታሪካዊ ቦታ ግን አላጋጠመኝም።
በዛሬ የቶሮንቶ የጉዞ ማስታወሻዬ ሁለተኛ ክፍል የምወስዳችሁ መቀመጫዬ ከሆነችው ቶሮንቶ በ140ኪ.ሜ ርቀት ውስጥ ስለምትገኘው ወይም ከ1:30-2:00 የመኪና ጉዞ ስለምትፈጀው ከ20-30 ሚሊዮን ቱሪስትች ስለሚፈሱባት Niagara እና በውስጧ ሸሽጋ ስለያዘቻቸው ታሪኮቿና ውበቶቿ ከታዘብኳቸው ሁለቱን አስደናቂና ተዓምራዊ የሚመስሉ ትዝብቶቼን መዝዤ ላጋራችሁ ፊታችሁ ቆሜያለሁ፤
ጊዜአችሁን እንድታውሱኝም ፍፁም አክብሮት በተሞላ ትህትናም እጠይቃለሁ።
♦️እንደ መንደርደሪያ
Niagara የካናዳ የውበት እና የታሪክ ምስጢርን የተሸከመች ልዩ ከተማ ናት፤ የሚያስደንቅ የውሃ ፏፏቴዋ ብቻ ሳይሆን በውስጧ ሸሽጋ የያዘቻቸው ታሪካዊ ቅርሶች፣ የተፈጥሮ ውበት እና የሰው ፈጠራ በአንድ ላይ የተዋሃዱባት ልዩ ቦታም ናት።
እያንዳንዱ አካባቢዋ እንደ ታሪክ መጽሐፍ እየተገለፀ የሚነበብ ሲሆን፣የሚያስደንቅ ውበቷ ደግሞ የሚጎበኙትን ሁሉ በአድናቆት አንድ ቋንቋ እንዲናገሩ የሚያስገድድ አንዳች ምስጢራዊ ኃይል ያላት ከተማም ናት።
በNiagara ያደረግሁት ጉብኝት የውሃ ፏፏቴውን አስደናቂ ግርማ ከማየት ባለፈ የልብን ጥልቅ ስሜት የሚነኩ ቦታዎችን የማውቅበት ዕድል ፈጥሮልኛል፤ከእነዚህም መካከል የካናዳ ምንአልባትም የተረጋገጠ መረጃ ባይገኝም የዓለማችን ትንሿ ቤተክርስቲያን እና የካናዳ ትልቁ የአበባ ሠዓት(Floral Clock)በልዩ ሁኔታ ቆይታዬን ቢቆጣጠሩትም በፅሁፉ ርዝማኔ የተከበሩ አንባቢዎቼ እንዳይሠላቹብኝ የጉዞ ማስታወሻዬ ለዛሬ በካናዳ ትንሿ ቤተክርስቲያን ላይ ማነጣጠርንና የካናዳ ትልቁ የአበባ ሠዓት(Floral Clock)ን የክፍል ሶስት ማሳደርን መርጫለሁ።
በክፍል ሁለት የጉዞ ማስታወሻዬ ከኒያግራ ውበት ጀርባ የተደበቀውን የተፈጥሮ ታሪክ ላካፍላችሁ ወድጃለሁ፤ ይህን ተሞክሮ ከእናንተ ጋር መጋራቴም ደስታን ስለሚያሳፍሠኝ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቅርቤዋለሁ።
♦️ስድስት ሠው ስለምታስተናግደው፣ስድስት የእንጨት ወንበርና ሁለት መፅሐፍ ቅዱስ ስላሏት የካናዳ ትንሿ ቤተክርስቲያን
ስለዚህች ቦታ ብዙ ብል ደስ ይለኛል
“በNiagara ውስጥ የተደበቀችው ትንሽ የሰላም ቤተክርስቲያን” ወይም“በተፈጥሮ ውበት መካከል ያለችው ትንሽ ቅዱስ ቦታ”አሊያም“Niagara ፏፏቴ አጠገብ ያለች የሰላም ቤት”
አዎን እነዚህ ሁሉ ቃላትችን ብደረድር በትክክል ሊገልጿት ይችላሉ ብዬ አላምንም፤ምክንያቱም ትንሿ ቤተክርስቲያን ከቃላቶች በላይ እጅግም ትልቅ ናትና።
በኒያግራ ፎልስ ያለችው በፈረንጆች አፍ Living Water Wayside Chapel ተብላ የምትታወቀው ትንሿ ቤተክርስቲያን ከፏፏቴው በግምት ከ7–10 ኪ.ሜ ገደማ፣
በመኪና ደግሞ ከ10–15 ደቂቃ በ Niagara Parkway በኩል ወደ ሰሜን በመጓዝ የምትገኝ በአጠቃላይ ከፏፏቴው ብዙ የማትርቅ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ናት፤ትንሿ ቤተክርስቲያን መቼ እንደተመሠረተች በርካቶች ስምምነት ላይ ለመድረስ ቢቸገሩም በኒያግራ አካባቢ ባለው የክርስቲያን ሪፎርምድ ቤተክርስቲያን (Niagara Falls Christian Reformed Church) በ1964 ዓ.ም በእምነት እጆች እንደተመሠረተች ታሪክን አጣቅሠው ይናገራሉ።
በወቅቱ ትንሿ ቤተክርስቲያን ስትመሠረት ዋነኛ ዓላማዋም በኒያግራ የሚያልፉ ቱሪስቶችና ተጓዦች ለጸሎት፣ለእረፍት እና የመንፈስ ምግብ ለማግኘት የሚቆሙባት፣በርካታ ጋብቻዎችም የሚፈፀሙባት ቅዱስ ቦታ እንደሆነችም የታሪክ መዛግብት እራሳቸው አፍ አውጥተው ይነግሩናል ።
♦️የትንሿ ቤተክርስቲያን አመሠራረት
በመጀመሪያ በዋልከር ቤተሰብ እርሻ ላይ ተገንብታ እንደነበር የሚነገርላት የካናዳ ትንሿ ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውራ ከቆየች በኋላ በ2012 እንደገና ወደምትገኝበት ቦታዋ ተመልሳ ታድሳ ቆማለች።
♦️የቤተክርስቲያኗ ስፋት
በግምት 10–15 ሜትር ካሬ (square meters)ትሆናለች፤አንድ ትንሽ ክፍል ቤት ያላትን መጠን መያዟ በካናዳ ትንሿ የእምነት ቦታ የሚል ስያሜን አጎናፅፎታል፤ይህች በካናዳ ትንሿ ቤተክርስቲያን ለጥቂት ሰዎች ብቻ ቦታ ቢኖራትም፣በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ጎብኚዎች በልባቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የያዘች መንፈሳዊ ቦታ ሆናለች።
♦️የቤተክርስቲያኗ ሀብቶች(ንብረቶች)
የኒያግራ፣የካናዳ ምንአልባትም የዓለም ትንሿ ቤተክርስቲያን ውስጥ ወርቅ ወይም ውድ ጌጥ አይገኝም፤ ነገር ግን ከሁሉ የሚበልጥ ሀብት ተደብቆባታል፤እሱም እጅግ ውዱና ገንዘብ የማይገዛው ሰላም። የLiving Water Wayside Chapel ትንሿ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው ነገር በመጠኑ ትንሽ ቢሆንም በትርጉሙ ግን እጅግ ትልቅ ነው፤ትኩር ብለህ ስትመለከት በእርግጥም ትንሽ ሕንፃ እንጂ ትልቅ መንፈሳዊ ታሪክ የያዘች ቦታ መሆኗን ትገነዘባለህ፤በተረት መጽሐፍ ውስጥ የተሳለች ነጭ ቤትም ትመስላለች፤ነገር ግን በውስጧ የሚኖረው ሰላም ከመጠኗ እጅግ የሚበልጥ ነው፤
በውስጧ አራት ትንንሽ የእንጨት ወንበሮች፣ ሁለት መጽሐፍ ቅዱሶች እና ጎብኚዎች ስማቸውንና መልዕክታቸውን የሚጽፉበት የእንግዶች መዝገብ አለ፤ቦታው ለስድስት፣አንዳንዴም ለአስር ምዕምናን ብቻ የሚበቃ ቦታና ስድስት የእንጨት ወንበሮች ቢኖሩትም ለሰላም፣ለጸሎት እና ለማሰላሰል የሚያስፈልገው ብዙ ነገር ግን በውስጡ ይዟል።
♦️ታሪክን የተሸከሙት በቁጥር ትንሽ የሆኑት የእንጨት ወንበሮቿና መፅሐፍ ቅዱሶቿ
በቁጥር ትንሽ የሆኑት የእንጨት ወንበሮቿ የጸሎት ታሪኮችን ይሸከማሉ፣መጽሐፍ ቅዱሶቿ ደግሞ ተስፋን ይሰብካሉ፤ የእንግዶች መዝገቧ ደግሞ ከዓለም ሁሉ የመጡ ልቦችን በአንድ ገጽ ላይ ያገናኛሉ፤በዚህም በውስጧ ሸሽጋ የያዘችው እንጨትና ወረቀት ብቻ እንዳልሆኑ ይልቁንም፤ ጸጥታ፣ ተስፋ፣ እምነት እና የሰው ልብ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።”
♦️ትህትናን መማር ከመግቢያ በሩ ይጀምራል
የኒያግራ ትንሿ ቤተክርስቲያን
Living Water Wayside Chapel
ወደ ውስጧ ለመግባት ትንሽ አንገትን ዝቅ ማድረግን፣ ከወገብ ማጎንበስን ይጠይቃል፤ የዚህ ምክንያቱ የበሩ ማነስ ብቻ አይደለም፤ይህም እንደ ሰላምታና ትህትና ዝቅ ማለትንም ጨምሮ ያስተምራል። በውስጧ ያሉት ትንንሽ ወንበሮች፣ ጸጥ ያለው አየር እና የጸሎት መንፈስ ሰዎችን ከውጪው ጫጫታ አርቀው ወደ ውስጣዊ ሰላም ይመሩታል።
ከኒያግራ ፏፏቴ ኃይልና ግርማ በኋላ የምትገኘው ይህች ትንሽ ቤተክርስቲያን ሰላምን በሹክሹክታና ቀልብን በሚገዛ የለሆሳስ ድምፅ ትሠብካለች።
🙏የታሪካዊ ጉዞዬ ባለውለተኞችን ዝቅ ብዬ አመሠግናለሁ
ይሄ በአእምሮዬም ለሰከንዶች እንኳን ውልብ ያላለው ወርቃማው የጉብኝት ዕድሌ ዝም ብሎ አልመጣም፤ለዜጋቸው የሚጨነቁ በበጎ ጉዳይ ከፊት የሚሠለፉ ደጋግ ሠዎች አሉ፤እነሱን ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለሁ፤
🙏ምስጋና ቁጥር 1
ይሄን ታላቅ ሠው እንዴት እንደማመሠግነው አላውቅም፤የትኛውስ ቃል የልቤን የውስጤን የመግለፅ አቅምም እንዳላቸውም ማወቅ ማወቅ ተስኖኛል፤”እኔ ምግብ ሳይሆን ለተከታዮችህ የምታጋራው ታሪክ ነው የምመግብህ”ብሎ ዕድሜ ዘመኔን ስዘክረው የምኖረው ታሪክን ከኒያግራ ፎልስ አፍሼ እንድመለስ ገንዘቡን ከስክሶ ላመቻቸልኝ በህግ ሙያው በካናዳ ሠማይ ስር አንቱታን ያተረፈው፣ለኢትዮጵያዊያን ችግር ፈጥኖ ደራሹና በካናዳ የሀገር መመኪያ(ኩራት) የሆነው ተክለሚካኤል አበበን ከስጦታዎች ሁሉ ለላቀው ስጦታህ ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ፣ከወገቤ ዝቅ ብዬ እጅ እነሳለሁ፤
🙏ምስጋና ቁጥር 2
ለትሁቱ፣ዝቅ ማለትንና ኢትዮጵያዊ ፍቅርን ያለስስት ለሚሠጠው ለልበ ቀናው የተዋጣለት YeHa Niagara Tours አስጎብኚ(Tour Guide)በዕድሜ ትንሹ በስራው ግዙፉን ካሌብን አመሠግናለሁ፤በማይሰስት የደግነት እጁ ጋብዞ፣ታሪክ አጋርቶ፣ በታሪክና በትውስታ የተሞላ የኒያግራ ፎልስን ዘመን የማይሽረው አስደሳች ቆይታ እንዲኖረኝ በማድረጉ አንደኛው የታሪኬ አካል አድርጌ እወስደዋለሁ፤ካሌብ በTour Guide ራሱን ያዘመነ አብረውኝ የተጓዙትን ከአሜሪካ ቴክሳስ የመጡ ሁለት ቱሪስቶችን ጭምር እንደ ኒያግራ ፎልስ ፏፏቴ በሚፈሠው አተራረኩና ልቅም ባለው አንደበቱ እጃቸውን በግርምት አፋቸው ላይ የሚጭኑ ከ2,000 በላይ ቱሪስቶች በስራ ብቃቱ ዙሪያ Very Excellent የሚል ሙሉ ነጥብ የሠጡት የሀገር መመኪያ የሆነ ባለሙያ ነውና ከኃላፊነትህ ውጪ እንደ ካሜራ ባለሙያ በመሆን ጭምር ዝቅ ብለህ ስሌገለገልከኝ አንተን ማመስገኛ ቃላት የለኝም፤ባለህበት ክበርልኝ።
👉NB.በክፍል ሶስት የጉዞ ማስታወሺያዬ ተዓምረኛውንና አስገራሚውን ትልቁን የካናዳ ሠዓት(Floral Clock)ብዙ ዙሪያ ብዙ የማጋራችሁ ነገር አለ ምሽት 1:30 ጠብቁኝ።
