የቀኝ አክራሪ የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ውይይትን በተመለከተ ሀገራቸዉ የድርድሩ አካል አይደለችም ብለዋል።ለእስራኤሉ ጦር ሬዲዮ እንደተናገሩት “እነሱ ለእኛ ትርጉም የለሽ ናቸው ፤ በሊባኖስ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መስራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
“ሂዝቦላ ሊባኖስ ውስጥ እስካለ ድረስ በሊባኖስ ከሚገኘው የፀጥታ ቀጠና እስራኤል መውጣት አይኖርበትም” ሲሉ ስሞትሪች አክለዋል።“ሂዝቦላህ መሳሪያውን እስካላወረድ ድረስ ብቻም ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ቡድኑ እስኪፈርስ ድረስ ጦራችንን ከሊባኖስ አናስወጣም” ሲሉም ተደምጠዋል።
“እኛ የምንፈልገው ሄዝቦላህ መሳሪያውን እንዲጥል ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ እንዲፈርስ፣ በሊባኖስ ውስጥ የመንግስት አካል እንዳይሆን እና እስራኤልን የሚያሰጋ ወታደራዊ ሃይል እንዳይኖረው ነው” ብለዋል።
ይህ አስተያየት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በተደረገው የመግባቢያ ስምምነት እና በሊባኖስ ግንባር ላይ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያላቸውን አንድምታ አስመልክቶ በእስራኤል የፖለቲካ እና የጸጥታ አካላት መካከል ውዝግቦች እያደጉ በመጡበት ወቅት የተሰጠ ነው።
ከመጋቢት 2 ጀምሮ በሊባኖስ bእስራኤል ጥቃት የተነሳ ከ4,100 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ12 ሺ በላይ ሰዎች ቆስለዋል ሲል የሊባኖስ መንግስት ይፋዊ መረጃ ያሳያል።እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ያሉ ቦታዎችን መያዟን ቀጥላለች፡፡
