በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ-ከተማ ወረዳ ሰባት ጌሾ ወንዝ እየተባለ በሚጠራዉ አካባቢ ዛሬ ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም 18 ሰው የጫነ ሚኒባስ ታክሲ ዋናውን መንገድ ስቶ ወንዝ ውስጥ በመግባቱ በተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ 18 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀው ከሆነ፤ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች በኮሚሽኑ አምቡላንስ እና በፖሊስ አምቡላንስ ወደ አቤት ሆስፒታልና አዲሱ ገበያ ጤና ጣቢያ ተወስደው ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
የአደጋ ጥሪዉ ለኮሚሽን መ/ቤቱ እንደደረሰ የአምቡላንስ አገልግሎት ቡድኑ በስፍራዉ ፈጥኖ በመድረስ በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች የከፋ ጉዳት ሳይደርስባቸዉ በሕይወት በማውጣትና የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና በመስጠት ወደ ሆስፒታል እንዲወሰዱ ማድረጉም ነው የተገለጸው።
ጉዳት ከደረሰባቸው ተጎጂዎች መካከል አንድ ነፍሰ ጡር ሴትና ወደትምህርት ቤት እየሄዱ ያሉ ተማሪዎች እንደሚገኙበት ያስታወቀው ኮሚሽኑ፤ የአደጋውን መንስዔ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን ፖሊስ እያጠራ እንደሚገኝ ገልጿል።
