ሀገራዊ የደሞዝ ጭማሪውን ምክንያት በማድረግ በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 54 የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን የሰቆጣ የከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት አስታዉቋል።
የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት አመረ እንደገለጹት በተለያዩ ጊዜያት ለንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ እየተፈጠረ የቆየ ቢሆንም ለመንግስት ሠራተኞች የተደረገውን የደሞዝ ጭማሪ ተከትሎ አንዳንድ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ያለምንም ምክንያት በተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ዋጋ እየጨመሩ መሆኑን የንግድ ጽ/ቤቱ ባደረገው ድንገተኛ የገበያ አሰሳ ማረጋገጥ ተችሏል።
በፋብሪካ ምርቶች እንደ የዘይት፣የስኳር፣የሳሙና እና የዕለት ተዕለት መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን እጥረት እንዳለ አድርጎ በማስወራት፣ ምርት የሚያሸሹ ፣ያለደረሰኝ የሚሸጡ እና የዋጋ ጭማሪ እንዳለ የሚያስመስሉ ነጋዴዎች እንዳሉም የጽ/ቤቱ ኃላፊው ገልጸዋል።
ከጸጥታ አካሉ ጋር በመቀናጀት በተደረገው የገበያ አሰሳ ከ196 ድርጅቶች በላይ ድንገተኛ ምልከታ መደረጉን የገለጹት አቶ ሙላት ጉብኝት ከተደረገባቸው የንግድ ድርጅቶች መካከል የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ፣ያለንግድ ፍቃድ እየነገዱ እና ያለደረሰኝ ሲሸጡ የተገኙ 54 የንግድ ድርጅቶች ታሽገዋል ።
በመንግስት በኩል ምንም አይነት የምርት አቅርቦት ችግር እንደሌለ እና በአስመጪዎች በኩል ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ እንደሌለ የገለጹት ኃላፊው ያለምንም ምክንያት መንግስት ሰራተኛው ደመወዝ ተጨምሮታል በሚል ሰበብ ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ዋጋ የጨመሩት ቸርቻሪ ነጋዴዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።ህገ ወጥነትን እና የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመከላከል የንግድ ግብረሃይሉ ቁጥጥር መጠናከር እንዳለበት በማንሳት ማህበረሰቡ ተረጋግቶ እንዲሸምት አሳስበዋል።
በህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት ድርጅታቸው የታሸገባቸው ነጋዴዎችም እንደየ ጥፋታቸው በማየት በንግድ አዋጁ መሰረት የተለያዩ ቅጣቶችን የሚቀጡ መሆኑን ጠቅሰው ከባድ ጥፋት ያለባቸውን ነጋዴዎችም ንግድ ፍቃዳቸውን በመሰረዝ ከንግድ መረቡ እስከማገድ ድረስ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል።
