7ኛው ሀገራዊ ምርጫ “ግልጽነት የጎደለው የምዝገባ አሠራር እየተከናወነ መሆኑን” ገለፁ

Date:

ስምንት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትላንት ጥር 15 ቀን 2018 ዓም ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ገና በዕጩዎች ምዝገባ ጅምሮ ላይ ሳለ “ሰላማዊውን የፖለቲካ ምህዳር የሚያጨልሙ ተግዳሮቶች” እያጋጠሟቸዉ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ ምርጫው “አሳታፊ፣ ሐቀኛ እና ተዓማኒ ሊሆን እንደማይችል” አሳስበዋል።

መግለጫውን ያወጡት ፓርቲዎች፣ ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር ኢትዮጵያ)፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ)፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ) ፣ አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አማራ ግዮናዊ)፣ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ናቸው።

ፓርቲዎቹ ባለፉት 30 ዓመታት የከሸፈውን ዲሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ለማስተካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቁርጠኝነት እንዲሠራ ቢጠበቅም፣ በአንጻራዊነት ከ1997ቱ ምርጫ ውጪ ሌሎቹ የነፃና ፍትሐዊ መመዘኛን ያላሟሉ መሆናቸውን አስታውሰዋል። አሁንም ገና ከምዝገባው ጅምር ላይ እየታዩ ያሉ ችግሮች በአስቸኳይ ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“የቀድሞው የደቡብ ክልል በአራት ክልሎች መከፈሉን ተከትሎ፣ ገዢው ፓርቲ በሲዳማ እና በሌሎቹ ሦስት ክልሎች ማለትም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልል በየምርጫ ክልሉ ከ5 እስከ 10 የክልል ምክር ቤት ዕጩዎችን ተቃዋሚዎች ባላወቁት መንገድ እንዲያስመዘግብ መደረጉን” ፓርቲዎቹ ገልጸዋል። ይህ ድርጊት የቦርዱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

ቦርዱ ያበለፀገው የዲጂታል ቴክኖሎጂ የምዝገባ ሥርዓትም ሌላው የፓርቲዎቹ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል። ፓርቲዎቹ እንደሚሉት፣ ሲስተሙን በቴክኒክ ደረጃ የመፈተሽ ዕድል አልተሰጣቸውም።

በተጨማሪም በምዝገባ ወቅት እንደ መስፈርት የቀረቡት የልደት ምስክር ወረቀት እና የዓይን እማኝ ማቅረብ፣ በተለይ ከከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ፈጽሞ የማይታሰቡ እና ተቃዋሚዎችን ከፉክክር ሜዳው ለማውጣት የታቀዱ “የፖለቲካ ሴራዎች” ናቸው ብለዋል።

ፓርቲዎቹ እያንዳንዱ ዕጩ የግል ኢሜይል እንዲኖረው መገደዱ እና አንድን ኢሜይል ከአንድ በላይ ዕጩዎች እንዳይጠቀሙ መከልከሉ አግባብነት የሌለውና ከሀገሪቱ የቴክኖሎጂ አቅም ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ጠቅሰዋል። የአካል ጉዳተኞችም የአካል ጉዳታቸው እየታየ ከሁለት ሆስፒታሎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸው አላስፈላጊ እንግልት መሆኑን ገልጸዋል።

በምዝገባ ወቅት የሚታየው የኢንተርኔት ኔትወርክ መቆራረጥ እና ለፋይዳ መታወቂያ ትሥሥር የተሰጠው የ3 ደቂቃ ጊዜ እጅግ አዳጋች መሆኑን የገለጹት ፓርቲዎቹ፤ ይባስ ብሎም ዕጩዎች ያለ ፓርቲያቸው ዕውቅና በስልካቸው ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲሰርዙ (declaim) የሚያስችል አማራጭ መኖሩ፣ “ገዢው ፓርቲ ዕጩዎችን በማስፈራራት ወይም በጥቅማ ጥቅም ለማስለቀቅ የተጠቀመበት ዘዴ ነው” ሲሉ ከሰዋል።

መንግሥት ከተጽዕኖ የጸዳ ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ እንዲያመቻች የጠየቁት ፓርቲዎቹ፤ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሐቀኛ ድርድር እንዲያደርግ እና ከታጠቁ ኃይሎች ጋር የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ በመድረስ የዜጎችን ደህንነት እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።

በመጨረሻም፣ ምርጫው በታሪክ የተሻለ እንዲሆን ለቀረቡት ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቁት ፓርቲዎቹ፤ ሲቪል ማኅበራት፣ ሚዲያዎች እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ10 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ጥቅምት 12 ቀን 2019...

ዳሸን ባንክ እና ሼባ ማይልስ የፕላቲንየም ብራንድ የማስተር ካርድ ይፋ አደረጉ

ዳሸን ባንክ እና ሼባ ማይልስ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ደንበኞች የፕሪሚየም...

የአሜሪካ የደህንነት ኃላፊ ኢራንን አስጠነቀቁ

ቡሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጄይ ክላይተን አርብ ዕለት ኢራን በውጭ...

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ  በአመት ከ1.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ታጣለች

85 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርናው ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን...