በስመ አብ፥ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ዱ አምላክ አሜን!
“የእግዚአብሔርም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ነበረ። የእግዚአብሔርም ቤት ሥራም ተፈጸመ፤”
(መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ፰፤፲፮)።
የደሴ ደብረ ሣሕል ቅዱስ አማኑኤል ሕንፃ ቤተመቅደስ በብፁዕ አባታችን፣ በአቡነ አትናቴዎስ ተባርኮ ኅዳር 02 ቀን 2012 ዓ.ም ሥራው ተጀምሮ ላለፉት 5 ዓመታት በቅዱስ አማኑኤል ፈቃድ ሲካሄድ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ባጋጠሙን ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት፤
፩ኛ. ሥራውን እንደተጀመረ የኮቪድ በሽታ መከሰቱ፤
፪ኛ. የሰሜኑ የእርስ በርስ ጦርነት መከሰት እና፤
፫ኛ. በሌሎች ተያያዥ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች የተነሳ ይህ በብዙ የተደከመበት የቅዱስ አማኑኤል ቤተመቅደስ ከዚህ ደረጃ ደርሶ ቆሞ ነው የምናየው፡፡
ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው እስካሁን ድረስ በአካባቢው የሚገኙ ምእመናን በማስተባበር ሥራውን እዚህ ያደረሰው ቢሆንም ይህን የቅዱስ አማኑኤል ሕንጻ ቤተመቅደስ ከፍጻሜ ላይ ለማድረስ በአገር በውስጥና በውጪ ሀገራት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን እገዛችሁ፤ ዕርዳታችሁ የሚያስፈልግበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል።
ከአሁን በፊት የኦን ላይን የገቢ ማሰባሰቢያ ኘሮግራም ብናዘጋጅም የተጠበቀውን ያህል ገንዘብ አላገኘንም፤ ቢሆንም በቅዱስ አማኑኤል ቸርነት በምእመናን ልግስና ሥራው አሁንም ቀጥሏል። አሁን ላይም የጥርብ ጌጠኛ ድንጋይ ለመገንባት ከ10,000,000.00 ብር/አስር ሚሊዮን በላይ ያስፈልገናል።
ስለሆነም የደሴ ቅዱስ አማኑኤል ሕንጻ ቤተመቅደስ ግንባታን ወደ ፍጻሜው ለማድረስ ሲባል ሐምሌ 06 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት በአዲስ አበባ መስቀል ፍላወር አካባቢ ቱሊፕ ኦሎምፒያ ሆቴል የእራት እና የኦን ላይን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር አዘጋጅተናል።
በመሆኑም የኢትዮጵያዊነት/የሰው ልጅነት ፍቅርና ክብር፤ ሰላምና አንድነት፤ የሃይማኖት መዋደድና መከባባር ተምሳሌት በሆነችው በወሎዋ የደሴ ከተማ እየታነጸ ላለው የቅዱስ አማኑኤል ቤተመቅደስ በአገር ውስጥና በውጪ አገራት ያላችሁ የእግዚአብሔር ልጆች አብራችሁን ትሆኑ ዘንድና የፍቅር ስጦታ እጃችሁን ትዘረጉልን ዘንድ በቅዱስ አማኑኤል ስም እንለምናችኋለን።
የደሴ ደብረ ሣሕል ቅዱስ አማኑኤል ሕንፃ ቤተመቅደስ አሠሪ ኮሚቴ።
