የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ በመቄት ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰበትን የገረገራ ቀራንዮ መድኀኔዓለም አቡነ ተክለሃይማኖትና አባ ሳሙኤል አንድነት ገዳም አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ትናንት ጎብኝተዋል።
ብፁዕነታቸው በአደጋው የተጎዳውን ቤተክርስቲያን ከተዘዋወሩ በኋላ ከወረዳው ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከሰበካ ጉባኤ አባላት እና ከሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባላት ጋር ጥልቅ ውይይት አድርገዋል።
የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴው በበኩሉ፣ ቤተክርስቲያኑ የደረሰበትን ጉዳት ተከትሎ በርካታ ወገኖች በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት እያደረጉት ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አስረድቷል።
በተጨማሪም፣ የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አብራርተዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ የቤተክርስቲያኑ ሁኔታ በመገናኛ ብዙኃን ከሚገለጸው በላይ አሳሳቢና አስቸኳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም፣ በሰለጠኑና ልምድ ባላቸው የምህንድስና ባለሙያዎች ድጋፍ፣ ጊዜያዊና በጥናት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ አባታዊ የሥራ መመሪያ አስተላልፈዋል።
ይህ ጉብኝትና የተላለፈው መመሪያ፣ የጥንታዊቷን ገዳም መልሶ ለመገንባትና ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት
