ባለፉት 45 ቀናት ብቻ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች 77 ሹፌሮች እና ረዳቶቻቸው ሲታገቱ 34 ሹፌር፣ ረዳት እና ተሳፋሪዎች ደግሞ መገደላቸውን ስሜ አይጠቀስ ያሉ የጣና አሽከርካሪዎች ማህበር አባል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ስሜ አይጠቀስ ያሉ የማህበሩ አባል መረጃውን ያጋሩት ባለፉት 45 ቀናት ወደ “የሾፌሮች አንደበት” ገጽ የመጡ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሾፌር፣ ረዳት እና ተሳፋሪዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ብቻ ነው።
” በየቦታው ሹፌሮች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የግፍ ውድድር ይመስላል ይህ ሁሉ ጥቃት የሚፈጸመው ሁሉም ሰው በአካባቢው የሚፈጸመውን ጥቃት ማውገዝ ባለመቻሉ ነው ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
አክለውም ” ይፋ ያደረግነው መረጃ ወደ ገጹ የመጣውን ብቻ እንጂ ሙሉ የጥፋቱን መጠን አያሳይም ነው ” ያሉት።
” የተጠቀሰው ቁጥርም ባለፉት 45 ቀናት ወደ ገጹ የመጣውን ብቻ ነው ወደ ኋላ ብንሄድ ከእዚህም ከፍ ያለ የሟች እና የተጎጂዎች ቁጥር ይፋ ማድረግ ይቻላል ” ሲሉ አክለዋል።
ማህበሩ ባጋራው መረጃ ፦
➡️ በ03/10/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከጎንደር ደባርቅ መሀከል 44 የሚባል ቦታ ላይ 2 ሹፌሮችን ከእነ ረዳቶች ታፍነው ተወስደዋል።
➡️ በ04/10/2017 ዓ/ም በአፋር ክልል ገዳማዊቱ አካባቢ አንድ ህዝብ ጫኝ አውቶብስ በጥይት ተመቶ የ1 ተሳፋሪ ህይወት አልፏል።
➡️ በ03/10/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከጃዊ ወደ ፓዊ ሲጓዝ ከጃዊ ትንሽ ወጣ ብሎ የነበረ ሲኖ ተሳቢ ሹፌሩን እና ረዳቱን አግተው ወስደዋል።
➡️ በ04/10/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን ፈለገ ብርሀን ወጣ ብሎ ጭየ የሚባል አካባቢ 1 የ fsr አሽከርካሪ በታጠቁ አካላቶች በጥይት ተመቶ ተገድሏል።
➡️ በአፋር ክልል በአዳይቱ እና ገዋኔ መሀል ባለችው ያንጉዲ የሚባል ኬላ ያለበት ቦታ ላይ አንድ አባዱላ ሚኒባስ ሹፌር በጥይት ተመቶ ህይወቱ አልፏል።
➡️ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን በቡለን ወረዳ ሰኔ 9/10/2017 ዓ/ም 9 ሹፌር ረዳቶች ታግተው ተወስደዋል።
➡️ በ14/10/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ማርቆስ እና አማኑኤል መካከል 1 ሹፌር ከነረዳቱ ታግተው ተወስደዋል።
➡️ በ16/10/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከመተማ ጎንደር መንገድ መቃ ላይ 6 ሹፌር እና ረዳቶች ተገድለዋል።
➡️ በ18/10/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከሶሮቃ አብረሀጂራ መንገድ እርጎየ አካባቢ 3 የኦባማ 2 የ FSR ሹፌሮች ከእነ ረዳቶቻቸው በድምሩ 10 ሹፌር እና ረዳቶች በአጋች ዘራፊዎች ታግተው ተወስደዋል።
➡️ በ18/10 /2017 ዓ/ም በአብርሀጅራ መተማ በኮሩመር አድርገው እየሄዱ የነበሩ አሽከርካሪዎች ልዩ ስሙ ደለሎ አብደረግ ከሚባል ቦታ 1 ሹፌር ሲገደል 7 ተሳፍሪና ሾፌር ታፍነው ተወስደዋል።
➡️ በ18/10/2017 ዓ/ም ከጎንደር መተማ መንገድ 4 ሹፌር እና ረዳቶች ታፍነው ተወስደዋል።
➡️ ደብረ ብርሀን መስመር ከሰንቦ ወደ ምንጃር የሚያስወጣው መንገድ ሀገረ ማርያም ላይ 1 ሾፌሮች በ19/10/2017 ዓ/ም ተገድሏል።
➡️ በ23 /10/2017 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ኤክስካቬተር ጭኖ እየሄደ የነበረ ሎቤድ በኦሮሚያ ክልል ከነቀምቴ 5 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ በዘራፊ ወንበዴዎች ሹፌሩ ተገድሏል።
➡️ በኦሮሚያ ክልል ከያዩ ፊንጫ መንገድ በታጠቁ ወንበዴወች 1 አሽከርካሪ ተገድሏል።
➡️ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አንቦ ኣለፍ ብሎ ጌዶ ሚባል አከባቢ 1 አሽከርካሪ በሽፍቶች ተገድሏል።
➡️ በ02/11/2017 ዓ/ም አዲስ አበባ ጅማ መንገድ ጊቤ ላይ 1 ሹፌር ታፍኖ ተወስዷል።
➡️ በ11/11/2017 ዓ/ም ማክሰኝት እና እንፍራዝ መሀል አንድ ሹፌር በዘራፊ ወንበዴዎች ተገድሏል።
➡️ በ12/11/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከጎንደር መተማ መንገድ ሰራባ ዝቅ ብሎ ባለው የመንገድ ክፍል 6 የተሳቢ 1 የአይሱዙ ሹፌር እና ረዳቶች በዘራፊ ወንበዴዎች በድምሩ 14 ታግተው ተወስደዋል።
➡️ በ11 /11/2017 ዓ/ም ከመትሀራ ወለንጭቲ መሀል ወለንጪቲ መግቢያ 1 ሹፌር ታግቶ ተወስዷል።
➡️ በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን 14/11/2017 ዓ/ም መራይ ቢኮሎ መሀል አቦ መስክ 3 ሹፌር ከእነ ረዳት በድምሩ 6 ታፍነው ተወስደዋል።
➡️ አሰቦት እና አዋሽ መሀል ሚዛን መዳረሻ 2 ሾፌር እና ረዳት በድምሩ 4 ሰዎች ታግተው ተወስደዋል።
➡️ በ17/11/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከደባርቅ ጃናሞራ ጨነቅ ላይ አንድ አሽከርካሪ ላይ ግድያ ተፈፅሟል።
➡️ በ18/11/2017 ዓ/ም በአማራ ክልል ከአብርሀጅራ እርጎየ አሪዳ የሚባል ልዩ ቦታ 1 ሹፌር 1 ተሳፋሪ በድምሩ 2 ሰው ላይ ግድያ ተፈፅሟል።
➡️ 18/112017 ዓ/ም በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን ከመራዊ ቢኮሎ ሹፌር ከእነ ረዳቱ ታግቷል።
➡️ በ23/11/2017 ዓ/ም በኦሮሚያ ክልል ፍቸ ወጣ ብሎ 2 ሹፌር ከእነ ረዳት እገታ ሲፈፀምባቸው አንድ ሹፌር እና ተሳፋሪ ላይ ግድያ ተፈፅሟል።
@tikvahethiopia
