የአዲስ አበባ ፖሊስ ብሩክ ተስፋዬ አርአያ ወይንም በቲክቶክ ሥሙ (ቡራ ቡል) በመባል የሚታወቀው ግለሰብ፤ ቲክቶክ የተሰኘውን የተንቀሳቃሽ ምስል መለዋወጫ በመጠቀም በተደጋጋሚ ጊዜ ከህብረተሠቡ ሥነ ልቦና ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን እያስተላለፈ የሚገኝ በመሆኑ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተፈለግኩት ነው ሲል አስታውቋል፡፡
ተፈላጊው ነዋሪነቱ በየካ ክ/ከተማ ሲግናል የጋራ መኖሪያ ቤቶች መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፤ ከዚህ ቀደም በሕግ የተከለከለን “ካናቢስ” የተባለ አደንዛዥ ዕጽ ይዞ በመገኘት ወንጀል ክስ ቀርቦበት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 2ኛ አርቲዲ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የዋስትና መብት ከተፈቀደለት በኋላ በቀጠሮ ቀን ሳይቀርብ ተሰውሮ መቆየቱን ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱም በሌለበት ታሕሳስ 23 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ጥፋተኛነቱን በማረጋገጥ፤ በአንድ ዓመት ጽኑ እስራትና በአንድ ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን አመላክቷል።
ተከሳሹ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላም ራሱን በመሰወር በማህበራዊ ሚዲያ (ቲክቶክ) የቀጥታ ስርጭት በተደጋጋሚ ጊዜ ከሕብረተሠቡ ሥነ ልቦና ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን እያስተላለፈ የሚገኝ በመሆኑ ጭምር በፖሊስ እየተፈለገ ይገኛል ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አክሎም፤ ማህበራዊ ሚዲያ (ቲክቶክ)ን በመጠቀም የከተማዋን ሠላም ለማወክ እና በሕብረተሰቡ ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር በተደራጀ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች እንደማይታገስ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት “ፖሊስ በክትትል ከደረሰባቸው መረጃዎች በተጨማሪ የህብረተሰቡን ጥቆማ መነሻ በማድረግ በህብረተሰቡ እና በከተማችን ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር በማሰብ ቲክቶክን በመጠቀም የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያሰራጩ የነበሩ ኪሩቤል መላኩ፣ አህመድ ሻሂር፣ ምኺኤል አብይ፣ በረከት ዳንኤል እና አብዩ ደግአረገ የተባሉ አምስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች የመዲናዋ ነዋሪዎች ደህንነት ስጋት ውስጥ የሚከቱና ድርጊቱ በቸልታ ከታለፈም ትልቅ አደጋ ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ የድርጊቱን ፈፃሚዎች እንደማይታገስ ያስታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ፤ መሠል እንቅስቃሴ በሚያደርጉ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ ነን ባዮች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።
አሐዱ ራዲዮ
