በ3ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዛሬ ምሽት በአንፊልድ ሮድ ሊቨርፑል ከአርሰናል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ተጋጣሚዎች በተያዘው የውድድር ዓመት ዋንጫውን ያሳካሉ ተብለው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በአርኔ ስሎት እየተመራ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ለማሳካት የሚያደርገው ብርቱ ፉክክር ይጠበቃል፡፡
ሊቨርፑል በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ከቀላቀሉ የሊጉ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
ግብጻዊውን የፊት መስመር ተጫዋች ሞሃመድ ሳላህን ጨምሮ የፊት መስመሩ ጥሩ መሆኑ የሚነገርለት ሊቨርፑል በተከላካይ ክፍሉ ላይ ግን ክፍተት አለበት በሚል እየተተቸ ይገኛል፡፡
በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ያልቻለው ሊቨርፑል እስካሁን አራት ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡
ቡድኑ በሁለቱ ጨዋታ 7 ግቦችን በማስቆጠር የፊት መስመሩ ጠንካራ መሆኑን ማሳየት ቢችልም በአንጻሩ አራት ግቦችን በማስተናገዱ ተከላካይ ክፍሉ ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡
አሰልጣኝ አርኔ ስሎት እየተቆጠረባቸው ባሉት ግቦች የተከላካይ ክፍላቸው ይበልጥ መሻሻል እንዳለበት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ቦርንማውዝን በ2ኛ ሳምንት ደግሞ ኒውካስል ዩናይትድን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
ተጋጣሚው የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ልክ እንደ ሊቨርፑል ሁሉ በውድድር ዓመቱ ያደረጋቸውን ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ድል አድርጓል፡፡
አርሰናል በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በማንቼስተር ዩናይትድ በብርቱ ተፈትኖ ድል ያደረገ ሲሆን÷ በ2ኛ ሳምንት ደግሞ ሊድስ ዩናይትድ ላይ 5 ግብ በማስቆጠር አሸንፏል፡፡
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል በዚህ የውድድር ዓመት ለሊጉ ክብር ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ነው፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የሊጉን ዋንጫ ያጣው አርሰናል በዚህ የውድድር ዓመት ዋንጫውን ለማሳካት እና የበላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ራሱን አጠናክሯል፡፡
አርሰናል ከዚህ ቀደም ይነሳበት የነበረውን የፊት መስመር ችግር ለመፍታት በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በንቃት መሳተፉ ይታወቃል፡፡
ዛሬ 12 ሰዓት 30 ላይ በሚደረገው ጨዋታም በመከላከሉ ጥያቄ እየተነሳበት የሚገኘውን የሊቨርፑልን የተከላካይ ክፍል ይፈትናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሊቨርፑል ጠንካራው የፊት መስመር ከአርሰናል ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
ከዚህ ተጠባቂ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 10 ሰዓት ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከዌስትሃም ዩናይትድ እንዲሁም ብራይተን ከማንቼስተር ሲቲ ይገናኛሉ፡፡
አስቶንቪላን ከክሪስታል ፓላስ የሚያገናኘው የ3ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ በቪላ ፓርክ ምሽት 3 ሰዓት ላይ ይደረጋል፡፡
(ኤፍ ኤም ሲ)
