የእስራኤል ቀጠናዊ ትብብር ሚኒስትር የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃን ጎበኝተዋል።
የእስራኤል ቀጠናዊ ትብብር ሚኒስትር ጊላድ ሻድሞን እና በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶ/ር አቭረሃም ንጉሤ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ጉብኝት አድርገዋል።
ዲፕሎማቶቹ እስራኤል በሚገኘው ሴቭ ዘ ቻይልድስ ሀርት (Save the Child’s Heart) የበጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ጉብኝት እንዲሁም ውይይት ማድረጋቸው የማዕከሉ የኮምኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዊት እሸቱ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ. በ1995የተመሰረተው ሴቭ ዘ ቻይልድስ ሃርት የልብ ሕመም ያለባቸው ጨቅላ ሕጻናትን ህይወት ለመታደግ የሚሰራ አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ነው።
ይህ ግብረሰናይ ድርጅት በፕሮግራሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ60 በላይ ሀገራት ለሚገኙ ህጻናት በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወት አድን የቀዶ ጥገና እና የልብ ስራዎችን ሰጥቷል።
ከሕክምናው ባሻገር ዘላቂ የጤና እንክብካቤን በመገንባት ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሲሆን በርህራሄ እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር፤ የሕጻናትን ልብ በማከም ጤናማ እና ባለ ብሩህ ተስፋ እንዲሆኑ ዕድል እየሰጠ ይገኛል።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ጋር ባለፉት ከ30 በላይ አመታት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በየዓመቱ ታካሚ ሕፃናትን እና ቤተሰቦቻቸውን እስራኤል ሃገር በመውሰድ ሙሉ ወጪዎችን በመሸፈንና በማሳከም እንዲሁም ለድርጅቱ ሃኪሞች የትምህርት ዕድል በማመቻቸት እየሰራ ይገኛል ማለታቸውን ዶ/ር ዳዊት ተናግረዋል።
ይህን በማስመልከት የእስራኤል ቀጠናዊ ትብብር ሚኒስትር ጊላድ ሻድሞን፣ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶ/ር አቭረሃም ንጉሤ እና የስራ ባልደረቦቻቸው በልብ ማዕከሉ ጉብኝት እና ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የእስራኤል ቀጠናዊ ትብብር ሚኒስትር ጊላድ ሻድሞን ታካሚዋቹ ተሽሏቸው ትልቅ ቦታ በመድረሳቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፅዋል ።አክለውም ይህ በጎ ተግባር የሚበረታታ እንደሆነ እና ለወደፊትም የትምህርት እድል ለማመቻቸት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
አምባሳደር ዶ/ር አቭረሃም ንጉሤ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እና እስራኤል በሕክምና፣ በግብርና እና ቴክኖሎጂ በጋራ እንደሚሰሩ አንስተው ይህ ደግሞ ትልቅ ምሳሌ ነው ብለዋል።
ሴቭ ዘ ቻይልድስ ሃርት በባለፈው አመት 47 ሕፃናት በመውሰድ እያሳከመ እንደሚገኝ አንስተው፤ አሁን ላይ 26 ሕፃናት በሕክምና ሂደት ላይ እንደሚገኙ እና በዓመቱ መጨረሻ 53 ታካሚዎችን ለማሳከም መታቀዱንም አመልክተዋል።
የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ህሩይ አሊ ሴቭ ዘ ቻይልድስ ሃርት ስለሚያደርገው ድጋፍ በልብ ሕሙማኑ ስም አመስግነው ይህ ድጋፍ እንዳይለየን ሲሉ ጠይቀዋል። በመርሐ ግብሩ በልጅነታቸው በእስራኤል ሃገር ሕክምና ያገኙ ታካሚዎች እና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል።
