(በእውቀቱ ስዩም)
ለእናት አገሬ ወይ ቦንድ አልገዛሁ፥ ወይ ቦንብ አልወረወርሁ፥ እንዲችው ስማስን እድሜን ገፋሁት፤
ከሁሉ የሚቆጨኝ የሆነ ጊዜ ላይ፥ ሰፈራችን ውስጥ ሳምንቱን ሙሉ ውሀ እልም ብላ ጠፋች ፤ ሆድ ቢብሰኝ “ ከመሀል ከተማ ወስደው ነው እንዴ የሚገድቡት ?“ ብየ ያማረርሁትን ሳስበው እስካሁን ይጠጥተኛል ፤ በውነት ግሳጼ የሚገባኝ ግም-ጃ ለባሽ ሰው ሰው ነኝ ፤
አድምጡኝማ ! ቲክቶክ ላይ፥ አንድ ሰው፥ በእንካስላንትያ መዝገበቃላት ውስጥ ለማካተት የሚከብድ ስድብ ተሳድቦ “አንበሳ ይወርድለታል” ፤ በባንጻሩ እኛ ፌስቡል ላይ የምንቸከችክ ሰዎች “ አንበሳው !“ “አንበሲት” ከሚል ቃል ያለፈው ደመወዝ የለንም፤ ለነገሩ ተመስጌን ነው ! ይህንንስ ማን አየብን !
በቀደም አንድ ወጣት ፥ አገር አማን ነው ብሎ የእግረኛ መንገዱ ዳር የተተከለውን ሳር በዘመናዊ ማጭድ ሲያጭድ ፥ ያንድ ክፍለከተማ ህዝብ ከበብ አድርጎ ሲመሰጥበት የሚያሳይ ቪድዮ” Sura ገጽ ላይ አይቼ ነበር፤ መቼም አታምኑኝ ግን በቦታው ነበርኩ፤
“ጊዜው ካፍያ ነበር ትንሽ ጨለም ብሎ
‘አባቴ ሲጠራኝ እያለ ና ቶሎ !”
አንድ ጎብዝ ወጣት ፤ አገር አማን ብሎ-
-በዘመናዊ ማጭድ እያጨደ እያለ ቀና ሲል ሰው ሰፍ ብሎ ይሾፈዋል፤ መጀመርያ ምን አጠፋሁ ብሎ ተደናገረ፤ የህዝቡ አስተያየት የወቀሳ ሳይሆን የጉጉት መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀበትም፤ ወድያው ወጣቱ ከወዛደርነት ወደ ሰርከስ ባለሙያነት ተቀየረ፤ ማጭዱ የገጠር ወፍጮ ድምጽ ያወጣ ነበር፥ ወጣቱ ሂሊኮፍተር ሞድ ላይ አደረገው፤ ማጭዱን በእግሩ መሀል አድርጎ እንደ ማጂክ መጥረጊያ እየጋለበ ማጨድ ጀመረ፤
ተሰብስበው ከሚያዩት ሰዎች አንዱ “ ሞራል ያንሳል ወገን “ ብሎ ካስጨበጨበለት በሁዋላማ ፥ማን ይቻለው?! ከታጨደው ሳር ዘግኖ አድቦልቡሎ ጢባጢቤ መጫወት ጀመረ፤
ጭራሽ ቪድዮው ሶሻል ሚድያ ላይ ሲለጠፍ ብዙ ሺ ሰው ማየቱን አስተውያለሁ፤
ባለፈው ፥ “አዝናኝና አስተማሪ ቪድዮ ሰርቼ ፥ ጭኜ ተመልካች አጣሁ” እያልህ ስታንቧቅስ የነበርከው ዠለሴ ! ለምን አጨዳ አትጀምርም?
እንግዲህ፥ አጫጁ ሰሞኑን ስልካችን ላይ ይከሰትና፥
“ያጨዳውን ትእይንት ተመልክታችሁ የወደዳችሁት ከታች አንድ ቁጥር ጻፉልኝ፤ ነገ ደግሞ ስከምርና ስወቃ የሚያሳየውን እለጥፋለሁ፤ ላይክ ሼር ኮፒሊንክ ማድረጉ እንዳይረሳ “
