ወጋገን ባንክ አ.ማ. በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት ባስመዘገበው ታሪካዊ አፈጻጸም የአንድ አክሲዮን ትርፍ ወደ 46.10 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 3.85 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ73 በመቶ ዕድገት ያሳያል ተብሏል።
መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው 32ኛው የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው ባንኩ በበጀት ዓመቱ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን ብር 13.5 ቢሊዮን ገቢ ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፤ ይህም የ38 በመቶ እድገት እንደሆነ ተመላክቷል።
የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዲሹ ሁሴን እንደተናገሩት የባንኩን የተከፈለ ካፒታል ወደ ብር 20 ቢሊዮን ለማድረስ ከተላለፈው ውሳኔ በኋላ የተከፈለው ካፒታል የ37 በመቶ ዓመታዊ እድገት በማሳየት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ብር 7 ቢሊዮን ደርሷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት የ29 በመቶ ብልጫ በማሳየት ብር 84.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ተቀማጭ ገንዘብ ደግሞ 66.5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ከሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል።
ካፒታል ከባንኩ ያገኘዉ መረጃ እንደሚያሳየው የባለአክሲዮኖች ብዛት እኤአ እስከ ሰኔ 30፣ 2025 ድረስ ወደ 14 ሺህ 871 ማደረጉ እና ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር 53.5 ቢሊዮን ብር መድረሱ ያሳያል።
CapitalNews
