ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠናን ስምምነት ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት የሚያስችል ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ማቋቋሟን አስታዉቃለች።
ይህ ኮሚቴ ከ55 የአፍሪካ አገራት ጋር የ1.4 ቢሊዮን ሕዝብ እና የ3.4 ትሪሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ያለውን ግዙፍ የአህጉር ገበያ ለመጠቀም የሚያስችለውን እንቅስቃሴ በቅንጅት ይመራል ተብሏል።
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚመራው ይህ ኮሚቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን፣ የብሔራዊ ባንክን፣ የጉምሩክ ኮሚሽንን፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴርን እንዲሁም የግሉን ዘርፍ ተወካዮችን ጨምሮ ቁልፍ ተቋማትን ያካተተ ሲሆን፣ የትግበራ ሂደቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ንኡሳን ኮሚቴዎችንም አቋቁሟል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደገለፀዉ ፤ አገሪቱ ለትግበራ ዝግጅቷ ማጠናቀቂያ ከደረሱት ስራዎች መካከል 97% የሚሆኑት የታሪፍ መስመሮች በሂደት ወደ ዜሮ ታሪፍ እንዲወርዱ ተወስኗል ብሏል። በተጨማሪም የጉምሩክ ኮሚሽን ለኤክስፖርት የሚላኩ ምርቶች የምስክር ወረቀት የመስጠት ስራውን ማጠናቀቁን ለመረዳት ተችሏል።
CapitalNews
