በጋምቤላ ክልል በህዝቡና በፀጥታ ኃይሉ ጠንካራ ትብብር ሰላምን የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩ የተጀመረው በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በመድረኩ እንዳሉት ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ መደፍረስ በፀጥታ ሀይሉ እና በህብረተሰቡ ትብብር አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጋትሉዋክ ሮን በበኩላቸው በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚታዩትን አለመግባባቶች በውይይት በመፍታት ሰላምን ለማምጣት ሁሉም አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባም ዶክተር ጋትሉዋክ አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሽኔ አስቲን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የተፈጠረውን ድርጊት አመራሩና ህብረተሰቡ በጋራ ሊያወግዙት ይገባል ብለዋል።
የሚያለያዩን ነጠላ ትርክቶችን በመተው የጋራ የሚያደርጉ ገዢ ትርክቶችን ለማጽናት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው እርስ በእርስ መደማመጥና መግባባት ሲቻል ነው ብለዋል።
በመሆኑም በክልሉ አሁን ያለውን ሰላም ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የክልሉ መንግስት ሠላሙን በዘላቂነት ለማስቀጠል የህግ ማስከበር ስራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
(ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት / ታህሳስ 13/2018 ዓ.ም)
