ዝርወተ አጽሙ ለቅዱስ ጊዮርጊስ

Date:


አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ድርሰቱ “ፀሐይ ዘልዳ፣ ኮከብ ዘልዳ፣ ዘልዳ ንጉሥ ነዓ ጊዮርጊስ- የልዳው ፀሐይ፤ የልዳው ኮከብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ ና” በማለት የዘመረለትና ታላቅ ምስጋና ያቀረበለት ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘመነ ሰማዓታት

ከንጉሡ ዱድያኖስና ሰባ ነገሥት ሥጋውንና አጥንቱን አቃጥለው፣ ፈጭተው ዐመድ አድርገው ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የበተኑትን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ዳግም ያሥነሳው ጥር ፲፷ ቀን ነው፡፡ ይህንንም ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን “ዝርወተ ዐጽሙ” ስትል ሰማዕቱን አዘክራ ትውላለች፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡                                                                                                                                                                                                            ““የልዳው ፀሐይ፣ የልዳው የምሥራቅ ኮከብ”                                                                                                                                                                                                                                                 
ቅዱስ ጊዮርጊስ አባቱ አንጣስዮስ (ዘሮንቶስ) እናቱ ደግሞ ቴዎብስታ በመባል ትታወቃለች፤ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚወዱ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ የአባቱ አገር “ቀጰዶቅያ” የሚባል ሲሆን የእናቱ አገር ግድሞ ልዳ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፍልስጤም ቀጰዶቅያ ግዛት ስሙ ልዳ በሚባል ሀገር በ3ኛው መ/ክ/ዘ ተወለደ፡፡

ዐሥር ዓመት ሲሆነው አባቱ ዐረፈ፡፡ ቀጰዶቅያ በትንሹ ምሥራቃዊ እስያ ትገኝ የነበረች ከሮም ገናና መንግሥት በፊት በፋርስ መንግሥት ሥር የነበረች ናት፡፡ ልዳ በሐዲስ ኪዳን ከኢየሩሳሌም በስተምዕራብ ከኤማሁስ ቀጥሎ 15 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ ወንጌልን እየዞረ ያስተማረባት ቦታም ናት፡፡

/ሥራ. 9፣32 – 35/፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰባት ዓመት ተጋድሎውን ፈጽሞ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ጊዜ ሥጋው ያረፈው በዚሁ በልዳ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ “የልዳው ፀሐይ፣ የልዳው የምሥራቅ ኮከብ” እየተባለ ይጠራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሰዓታት በተባለው መንፈሳዊ ድርሰቱ “ፀሐይ ዘልዳ፣ ኮከብ ዘልዳ፣ ዘልዳ ንጉሥ ነዓ ጊዮርጊስ” በማለት የዘመረለትና ታላቅ ምስጋናም ያቀረበለት ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ትርጉሙም  “የልዳው ፀሐይ፤ የልዳው ኮከብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ ና” ማለት ነው፡፡                                                                                                                                                                                                                                                                       
ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ የተወደለበት ዘመነ ሰማዕታት ብዙ ክርስቲያኖች በመከራ የተፈተኑበትና ስለክርስትና ሃይማኖት ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ሕይወታቸውን ለሞት የሰጡበት ዘመን ነበር፡፡ በዚያም ዘመን ያንን አገር የሚመራውና የሚያስተዳድረው “ዱድያኖስ” የሚባል ከሐዲና ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ነበር፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት ዞሮንቶስ በዱድያኖስ ቤተ መንግሥት ታላቅ ሹመት ተሰጥቶት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ በዚያ ዘመንም አባት ሲሞት ልጁ በሥራው የመተካት መብት ስለነበር የሃያ ዓመት ዕድሜ የነበረው ወጣቱ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስም በአባቱ ሹመት ተተክቶ ለመሥራት ወደ ንጉሡ ሔደ፡፡

ንጉሥ ዱድያኖስ በቤተ መንግሥቱ ጣዖት አቁሞ ለጣዖት ሲሰግድና ሕዝቡንም ሁሉ እያስገደደ ለጣዖት እንዲሰግዱና ጣዖት እንዲያመልኩ ሲያደርግ በማግኘቱ ይህንን እኩይ ተግባር በመቃወም ገና በሃያ ዓመቱ የሰማዕትነት ተጋድሎውን ጀመረ፡፡                                                                                                                                                                                                                                              
የሰማዕቱ ተጋድሎና ምስክርነት                                                                                       

በእግዚአብሔር ላይ ባለው የፀና እምነት መሠረት የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ከንቱ መሆኑን በመገንዘብ ያለውን ሀብት ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በመስጠት  የዚህን ዓለም ክብር ሁሉ በመናቅ ከንጉሡ ከዱድያኖስና ሰባ ነገሥት በመባል ከሚታወቁት ኃያላን ጋር ተጋድሎውን ቀጠለ፡፡  ለሥጋዊ ሕይወቱም ሳይሳሳና ሳይፈራ በንጉሡ ፊት ቆሞ መሰከረ፡፡


ንጉሡና የእሱ ተከታዮች የሚሰግዱለት ጣዖትም ምንም ምን ማድረግ የማይችል ደካማ ፍጡር መሆኑን  ከአስረዳ በኋላ ሰማይና ምድርን፣ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ የፈጠረውን እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩና ለእሱም እንዲሰግዱ እያስተማረ የንጉሡን ሚስት ንግሥቲቱን ሳይቀር ሕዝቡን ሁሉ በማሳመን የሰማዕትነት ተግባሩን ቀጠለ፡፡

ከሐዲውና ጣዖት አምላኪው ዱድያኖስ በአምልኮ ጣዖት የፀና፣ እግዚአብሔርን የካደ ከመሆኑ የተነሣ፤ እሱ ቃሉን ሰምቶ በእውነተኛው አምላክ ማመን ሲገባው በተቃራኒው ቅዱስ ጊዮርጊስ እሱ ለሚያመልከው ጣዖት ቢሰግድና በእሱም ጣዖት ቢያመልክ ከአባቱ የበለጠ ሹመትና ክብር እንደሚሰጠውና ከእሱም ቀጥሎ ባለው የመንግሥት ሥልጣን ላይ እንደሚያስቀምጠው ደጋግሞ ቃል በመግባት ያባብለው ነበር፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን የእግዚአብሔርን እውነተኛ አምላክነት፣በሚገባ ያወቀ ከመሆኑም በላይ የዚህን ዓለም ከንቱነት ከልብ የተረዳ ስለሆነ የንጉሡ የዱድያኖስ ቃል አላታለለውም፣ ጊዜያዊ ሹመትና ሽልማትም አልማረከውም፡፡ እንዲያውም ሰባት ዓመት ሙሉ ተጋድሎውን በመቀጠል እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ የሆኑ ፀዋትወ መከራዎችን በመቀበል የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ምስከር ሆኖአል፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም በማድረግ ብዙ አሕዛብን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓል፡፡                                                                                                                                                                                                                                                     
ቅዱስ ጊዮርጊስም በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ፡፡ ቅዱሱንም እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን አሉት፡፡

በዚያን ጊዜ ጸለየ፤ እንዳሉትም አደረጋቸው፤ ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው በርካቶች በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ “በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ፤ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ” ብሎታል፡፡


ከሃዲው ንጉሥ ዱድያኖስ ግንድ አምጥተው ቅዱስ ጊዮርጊስን በግንዱ ላይ እንዲቸነክሩት አዘዘ፤ በላዩም ላይ ሰም አፍስሰው እሳት እንዲያነዱበት አደረገ፡፡ ከዚያም ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት፡፡ አቃጥለው፣ አሳርረው ሥጋውንና አጥንቱን ፈጩት፤ አንጀቱ ሁሉ ወጥቶ ከምድር ላይ እስኪዘረገፍ ድረስ አሰቃዩት፡፡ በዚህም ነፍሱ ከሥጋው ተለየች፡፡

የሰማዕቱን ሥጋ አቃጥለው ፈጩት አመዱንም በቀፎ አድርገው ደብረ ይድራስ በሚባል ተራራ ላይ በተኑት፡፡ “ደብረ ይድራስ” ማለት ምድረ በዳ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ጌታችንም የሰማዕቱን ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው፡፡ ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰበከ፡፡ በርካታ አሕዛብም ይህንን ታላቅ ተአምራት አይተው አምነዋል፡፡ በኋላም በሰማዕትነት አልፈዋል፡፡


እንደ ማጠቃለያ
“መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት በተናገረው ቃል መሠረት፤ በሃይማኖት ምክንያት መከራ እየተቀበለና ስለክርስቶስ እየመሰከረ በግፍ የተገደለ ሰው ሰማዕት ተብሎ ይጠራል፡፡

ይህ የቅድስናና የክብር ስም የሚገኘውም እንዲሁ በከንቱ ሳይሆን ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ከብዙ ተጋድሎና ፈተና በኋላ ነው/ሐዋ ሥራ. ፩፥፰፤ ፳፪÷፳፮/፡፡ ከእነዚህ ሰማዕታት አንዱ በየዓመቱ የሰባት ዓመት ተጋድሎውና የዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በስሙ በታነጹ አብያተ ክርስቲያት ሁሉ በታላቅ ክብር የሚከበርለት የልዳው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር ፲፰  ቀን “ዝርዎተ አጽሙ” በማለት ሰማዕቱን አዘክራ ትውላለች፡፡ በስሙ በታነጹለት አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ታቦተ ሕጉ ውጥቶ በደማቅ ሥነ ሥርዐት ተከብሮ ይውላል፡፡


            የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ አማላጅነትና  ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
                           ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዋቤ መጻሕፍት፡-
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ
✍️ መጽሐፈ ሰዓታት
✍️ መጽሐፈ ስንክሳር
✍️ የቤተክርስቲያን መዝገበ ቃላት

    እንኳን ለልዳው ፀሐይ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!! በመ/ር ጌታቸው በቀለ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በጡረታ ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ...

አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ አዲስ መግለጫ አወጣች

ታዋቂዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ለስፖርት ወዳጆችና ለደጋፊዎቿ ወቅታዊ መረጃ...

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...